Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


መዝሙር 57 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


መዝሙር 57
57፥7-11 ተጓ ምብ – መዝ 108፥1-5
ለመዘምራን አለቃ፤ “አታጥፋ” በሚለው ቅኝት የሚዘመር፤ ከሳኦል ፊት ሸሽቶ በዋሻ በነበረበት ጊዜ፤ የዳዊት ሚክታም።

1 ማረኝ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ ማረኝ፤ ነፍሴ አንተን መጠጊያ አድርጋለችና፤ በክንፎችህ ሥር እጠለላለሁ።

2 ለእኔ ያሰበውን ወደሚፈጽምልኝ አምላክ፣ ወደ ልዑል እግዚአብሔር እጮኻለሁ።

3 ከሰማይ ልኮ ያድነኛል፤ የረገጡኝን ያዋርዳቸዋል፤ ሴላ እግዚአብሔር ምሕረቱንና ታማኝነቱን ይልካል።

4 ነፍሴ በአንበሶች ተከብባለች፤ በሚዘነጣጥሉ አራዊት መካከል ወድቄአለሁ፤ እነዚህም፣ ጥርሳቸው ጦርና ፍላጻ፣ ምላሳቸውም የተሳለ ሰይፍ የሆኑ ሰዎች ናቸው።

5 እግዚአብሔር ሆይ፤ ከሰማያት በላይ ከፍ ከፍ በል፤ ክብርህም በምድር ሁሉ ላይ ትንሰራፋ።

6 ለእግሬ ወጥመድን ዘረጉ፤ ነፍሴንም አጐበጧት፤ በመተላለፊያዬ ላይ ጕድጓድ ቈፈሩ፤ ነገር ግን ራሳቸው ገቡበት። ሴላ

7 እግዚአብሔር ሆይ፤ ልቤ ጽኑ ነው፤ ልቤ ጽኑ ነው፤ እቀኛለሁ፤ እዘምራለሁ።

8 ነፍሴ ሆይ፤ ንቂ! በገናና መሰንቆም ተነሡ! እኔም ማልጄ እነሣለሁ።

9 ጌታ ሆይ፤ በሕዝቦች መካከል አመሰግንሃለሁ፤ በሰዎችም መካከል እዘምርልሃለሁ፤

10 ምሕረትህ እስከ ሰማያት ከፍ ብላለችና፤ ታማኝነትህም እስከ ሰማያት ትደርሳለች።

11 እግዚአብሔር ሆይ፤ ከሰማያት በላይ ከፍ ከፍ በል፤ ክብርህም በምድር ሁሉ ላይ ትንሰራፋ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos