Biblia Todo Logo
La Biblia Online

- Anuncios -


መዝሙር 148 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


መዝሙር 148

1 ሃሌ ሉያ። እግዚአብሔርን ከሰማያት አመስግኑት፤ በላይ በአርያም አመስግኑት።

2 መላእክቱ ሁሉ አመስግኑት፤ ሰራዊቱ ሁሉ አመስግኑት፤

3 ፀሓይና ጨረቃ አመስግኑት፤ የምታበሩ ከዋክብት ሁሉ አመስግኑት።

4 ሰማየ ሰማያት አመስግኑት፤ ከሰማያትም በላይ ያላችሁ ውሆች አወድሱት።

5 እርሱ ስላዘዘ ተፈጥረዋልና፣ የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑት።

6 ከዘላለም እስከ ዘላለም አጸናቸው፤ የማይሻርም ሕግ ደነገገላቸው።

7 የባሕር ውስጥ ግዙፍ ፍጥረትና ጥልቅ ውሆች ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ከምድር አመስግኑት።

8 እሳትና በረዶ፣ ዐመዳይና ጭጋግ፣ ትእዛዙንም የሚፈጽም ዐውሎ ነፋስ፣

9 ተራሮችና ኰረብቶች ሁሉ፣ የፍሬ ዛፎችና ዝግቦች ሁሉ፣

10 የዱር አራዊትና የቤት እንስሳት ሁሉ፣ በምድር የሚሳቡ ፍጥረታትና የሚበርሩ ወፎችም፣

11 የምድር ነገሥታትና ሕዝቦች ሁሉ፣ መሳፍንትና የምድር ገዦች ሁሉ፣

12 ወጣት ወንዶችና ደናግል፣ አረጋውያንና ልጆች ያመስግኑት።

13 ስሙ ብቻውን ከፍ ያለ ነውና፣ ክብሩም ከምድርና ከሰማይ በላይ ነውና፣ እነዚህ ሁሉ የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑ።

14 እርሱ ለሕዝቡ ቀንድን አስነሥቷል፤ ለቅዱሳኑ ሁሉ ምስጋና፣ እጅግ ቅርቡ ለሆነው ሕዝቡ፣ ለእስራኤል ልጆች። ሃሌ ሉያ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos