Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


መዝሙር 144 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


መዝሙር 144
የዳዊት መዝሙር።

1 እጆቼን ለጦርነት፣ ጣቶቼን ለውጊያ የሚያሠለጥን፣ እግዚአብሔር ዐለቴ ይባረክ።

2 እርሱ አፍቃሪ አምላኬና ጽኑ ዐምባዬ ነው፤ ምሽጌና ታዳጊዬ፣ የምከለልበትም ጋሻዬ ነው፤ ሕዝቤን የሚያስገዛልኝም እርሱ ነው።

3 እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህን ያህል በልብህ ስፍራ ትሰጠው ዘንድ ሰው ምንድን ነው? ታስበውስ ዘንድ የሰው ልጅ እስከዚህ ምንድን ነው?

4 ሰው እንደ እስትንፋስ ነው፤ ዘመኑም ፈጥኖ እንደሚያልፍ ጥላ ነው።

5 እግዚአብሔር ሆይ፤ ሰማያትህን ሰንጥቀህ ውረድ፤ ይጤሱም ዘንድ ተራሮችን ዳስስ።

6 የመብረቅ ብልጭታ ልከህ በትናቸው፤ ፍላጻህን ሰድደህ ግራ አጋባቸው።

7 እጅህን ከላይ ዘርጋ፤ ከኀይለኛ ውሃ፣ ከባዕዳንም እጅ ታደገኝ፤ አድነኝም።

8 አንደበታቸው ሐሰትን ይናገራል፤ ቀኝ እጃቸውም የቅጥፈት ቀኝ እጅ ናት።

9 አምላክ ሆይ፤ አዲስ ቅኔ እቀኝልሃለሁ፤ ዐሥር አውታር ባለው በገና እዘምርልሃለሁ።

10 ነገሥታትን ድል የሚያጐናጽፍ፣ ባሪያውን ዳዊትን ከሚጐዳ ሰይፍ የሚያድነው እርሱ ነው።

11 አንደበታቸው ሐሰትን ከሚናገር፣ ቀኝ እጃቸው የቅጥፈት ቀኝ እጅ ከሆነችው፣ ከባዕዳን እጅ ታደገኝ፤ አድነኝም።

12 ወንዶች ልጆቻችን በወጣትነታቸው፣ የተሟላ ዕድገት እንዳገኘ ተክል፣ ሴቶች ልጆቻችንም ቤተ መንግሥት ለማስጌጥ እንደ ተቀረጹ የማእዘን ዐምዶች ይሁኑ።

13 ጐተራዎቻችን በተለያየ የእህል ዐይነት፣ የተሞሉ ይሁኑ፤ በጎቻችን እስከ ሺሕ ይውለዱ፤ በመስኮቻችንም እስከ ዐሥር ሺሕ ይባዙ።

14 ከብቶቻችን ይክበዱ፤ አይጨንግፉ፤ አይጥፉም። እኛም በምርኮ አንወሰድ፤ በአደባባዮቻችንም ዋይታ አይሰማ።

15 ብፁዕ ነው፤ ይህ ባርኮት ገንዘቡ የሆነ ሕዝብ፤ ብፁዕ ነው፤ እግዚአብሔር አምላኩ የሆነ ሕዝብ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos