Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘኍል 4 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ቀዓታውያን

1 እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤

2 “ከሌዋውያን ወገን የቀዓት ዘር የሆኑትን በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው ቍጠሩ።

3 እንዲሁም በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ለማገልገል የሚመጡትን ከሠላሳ እስከ ዐምሳ ዓመት የሆናቸውን ወንዶች ሁሉ ቍጠሩ።

4 “በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የቀዓታውያን ሥራ ንዋየ ቅድሳቱን መጠበቅ ነው።

5 ሰፈሩ ሲነሣ አሮንና ልጆቹ ገብተው የሚከልለውን መጋረጃ ያውርዱ፤ የምስክሩንም ታቦት ይጠቅልሉበት፤

6 ከዚያም በአቆስጣው ቍርበት ይሸፍኑት፤ ሙሉ በሙሉ ሰማያዊ የሆነ መጐናጸፊያ በላዩ ላይ ይዘርጉበት፤ መሎጊያዎቹንም በየቦታው ያስገቡ።

7 “በገጸ ኅብስቱ ገበታ ላይ ሰማያዊ ጨርቅ ይዘርጉበት፤ በላዩም ላይ ወጭቶች፣ ጭልፋዎች፣ ጽዋዎች፣ ለመጠጥ ቍርባን የሚሆኑትን ማንቈርቈሪያዎች እንዲሁም ሁልጊዜ ከዚያ የማይታጣውን ኅብስት ያስቀምጡ።

8 በእነዚህም ላይ ቀይ ጨርቅ ይዘርጉ፤ የአቆስጣውን ቍርበት ደርበውም መሎጊያዎቹን በየቦታቸው ያስገቡ።

9 “ደግሞም ሰማያዊ ጨርቅ ወስደው ማብሪያ መቅረዙንና መብራቶቹን፣ መኰስተሪያዎቹንና የኵስታሪ መቀበያዎቹን፣ እንዲሁም ለዚሁ አገልግሎት የሚውሉትን የዘይት ዕቃዎች ይሸፍኑበት።

10 ከዚያም ይህንና ከዚሁ ጋራ የተያያዙትን ዕቃዎች ሁሉ በአቆስጣ ቍርበት መሸፈኛ ጠቅልለው በመሸከሚያ ሳንቃ ላይ ያስቀምጡት።

11 “በወርቅ መሠዊያ ላይ ሰማያዊ ጨርቅ ዘርግተው በአቆስጣ ቍርበት በመሸፈን መሎጊያዎቹን በየቦታቸው ያስገቡ።

12 “እንዲሁም በመቅደሱ ውስጥ ለአገልግሎት የሚሆኑትን ዕቃዎች በሙሉ ወስደው በሰማያዊ ጨርቅ በአቆስጣ ቍርበት በመሸፈን በመሸከሚያው ሳንቃ ላይ ያስቀምጡት።

13 “ከናሱ መሠዊያ ላይ ዐመዱን ጠርገው ሐምራዊ ጨርቅ ያልብሱት፤

14 ከዚያም ለመሠዊያው አገልግሎት የሚውሉትን ዕቃዎች በሙሉ፣ የእሳት ማንደጃዎቹን፣ ሜንጦዎቹን፣ የእሳት መጫሪያዎቹንና ጐድጓዳ ሳሕኖችን በላዩ ላይ ያድርጉ፤ በእነዚህም ላይ የአቆስጣ ቍርበት መሸፈኛ አልብሰው መሎጊያዎቹን በየቦታቸው ያስገቡ።

15 “አሮንና ልጆቹ መቅደሱንና ዕቃዎቹን፣ ንዋየ ቅድሳቱንም በሙሉ ሸፍነው ከጨረሱ በኋላ ሰፈሩ ለመንቀሳቀስ ዝግጁ ሲሆን፣ ቀዓታውያን ለመሸከም ይምጡ፤ እንዳይሞቱ ግን ንዋየ ቅድሳቱን መንካት የለባቸውም፤ ስለዚህ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ያሉትን እነዚህን ዕቃዎች የሚሸከሙ ቀዓታውያን ናቸው።

16 “የካህኑ የአሮን ልጅ አልዓዛር በመብራቱ ዘይት፣ ደስ የሚያሰኝ ሽታ ባለው ዕጣን፣ ዘወትር በሚቀርበው በእህል ቍርባንና በቅብዐ ዘይቱ ላይ ኀላፊነት ይኖረዋል፤ እንደዚሁም ማደሪያውንና በውስጡ ያለውን ሁሉ መቅደሱንና ዕቃዎቹን ጭምር ይጠብቃል።”

17 እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤

18 “የቀዓት ጐሣዎች ከሌዋውያን ተለይተው እንዳይጠፉ፤

19 ወደ ንዋየ ቅድሳቱ በሚቀርቡበትም ጊዜ በሕይወት እንዲኖሩ እንጂ እንዳይሞቱ አንተ ይህን አድርግላቸው፤ አሮንና ልጆቹ ወደ መቅደሱ ይግቡ፤ እያንዳንዱንም ሰው በየሥራው ላይ ይደልድሉት፤ ምን መሸከም እንዳለበትም ያስታውቁት።

20 ቀዓታውያን ግን ንዋየ ቅድሳቱን ለአንድ አፍታ እንኳ ለማየት አይግቡ፤ ቢገቡ ይሞታሉ።”


ጌድሶናውያን

21 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤

22 “ጌርሶናውያንንም በየቤተ ሰባቸውና በየጐሣቸው ቍጠራቸው፤

23 ከሠላሳ እስከ ዐምሳ ዓመት የሆናቸውን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ለማገልገል የሚመጡትን ወንዶች ሁሉ ቍጠር።

24 “የጌርሶናውያን ወገኖች የሥራና የሸክም አገልግሎታቸው ይህ ነው፤

25 እነርሱም የማደሪያውን መጋረጃዎች፣ የመገናኛውን ድንኳን፣ መደረቢያውንና በላዩ ላይ ያለውን የአቆስጣ ቍርበት፣ የመገናኛውን ድንኳን ደጃፍ መጋረጃዎች ይሸከሙ፤

26 እንዲሁም በማደሪያውና በመሠዊያው ዙሪያ ያሉትን የአደባባዩን መጋረጃዎች፣ የአደባባዩን ደጃፍ መጋረጃ፣ ገመዶችና ለዚሁ አገልግሎት የሚውሉትን ዕቃዎች ሁሉ ይሸከሙ፤ በዚህም ያገልግሉ።

27 የጌርሶናውያን አገልግሎት ሁሉ፣ ሸክምም ሆነ ሌላ ሥራ አሮንና ልጆቹ በሚሰጡት አመራር መሠረት ይሆናል። የሚሸከሙትን ሁሉ በኀላፊነት ታስረክቧቸዋላችሁ።

28 እንግዲህ የጌርሶናውያን ጐሣዎች በመገናኛው ድንኳን የሚኖራቸው አገልግሎት ይህ ነው፤ ተግባራቸውም በካህኑ በአሮን ልጅ በኢታምር አመራር ሥር ይሆናል።


ሜራሪያውያን

29 “ሜራሪያውያንን በየጐሣቸውና በየቤተ ሰቦቻቸው ቍጠራቸው፤

30 እንዲሁም በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ለማገልገል የሚመጡትን ከሠላሳ እስከ ዐምሳ ዓመት የሆናቸውን ወንዶች ሁሉ ቍጠር።

31 በመገናኛው ድንኳን ውስጥ አገልግሎቶቻቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜ ተግባራቸው ይህ ነው፤ የማደሪያውን ሳንቃዎች፣ መወርወሪያዎች፣ ምሰሶዎችንና መቆሚያ እግሮቻቸውን፣ ይሸከማሉ፤

32 እንደዚሁም በአደባባዩ ዙሪያ ያሉትን ምሰሶዎች ከነመቆሚያ እግሮቻቸው፣ ካስማዎችን፣ ገመዶችን፣ ከእነዚሁ ጋራ ያሉትን ዕቃዎች ሁሉና ማንኛውም ለአገልግሎቱ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ሁሉ ይሸከማሉ። እያንዳንዱ ሰው የሚሸከመውን ዕቃ ለይታችሁ በስሙ መድቡለት።

33 እንግዲህ የሜራሪያውያን ጐሣዎች በካህኑ በአሮን ልጅ በኢታምር ሥር ሆነው በመገናኛው ድንኳን ሲሠሩ አገልግሎታቸው ይህ ነው።”


የሌዋውያን ጐሣዎች ቈጠራ

34 ሙሴ፣ አሮንና የማኅበረ ሰቡ አለቆች ቀዓታውያንን በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው ቈጠሯቸው።

35 ከሠላሳ እስከ ዐምሳ ዓመት ሆኗቸው በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ለማገልገል የመጡት ወንዶች ሁሉ፣

36 በየጐሣቸው የተቈጠሩት ሁለት ሺሕ ሰባት መቶ ዐምሳ ነበሩ።

37 ይህ ከቀዓት ጐሣዎች ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ያገለገሉት ሰዎች ጠቅላላ ድምር ነው። ሙሴና አሮን፣ እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት እነዚህን ቈጠሯቸው።

38 ጌርሶናውያን በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው ተቈጥረው ነበር።

39 በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ለማገልገል የሚመጡት ከሠላሳ እስከ ኀምሳ ዓመት የሆናቸው ወንዶች ሁሉ፣

40 በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው የተቈጠሩት ሁለት ሺሕ ስድስት መቶ ሠላሳ ነበሩ።

41 ይህ ከጌርሶን ጐሣዎች በመገናኛው ድንኳን ያገለገሉት ሰዎች ጠቅላላ ድምር ነው፤ እግዚአብሔር በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ሙሴና አሮን እነዚህን ቈጠሯቸው።

42 ሜራሪያውያንም በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው ተቈጥረው ነበር።

43 በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ለማገልገል የሚመጡት ከሠላሳ እስከ ዐምሳ ዓመት የሆናቸው ወንዶች ሁሉ፣

44 በየጐሣቸው የተቈጠሩት ሦስት ሺሕ ሁለት መቶ ነበሩ።

45 ይህ የሜራሪ ጐሣዎች ጠቅላላ ድምር ነው፤ እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ሙሴና አሮን እነዚህን ቈጠሯቸው።

46 ስለዚህ ሙሴ፣ አሮንና የእስራኤል አለቆች ሌዋውያኑን በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው ቈጠሯቸው፤

47 ከሠላሳ እስከ ዐምሳ ዓመት ሆኗቸው በመገናኛው ድንኳን ውስጥ አገልግሎት ለመስጠትና ለመሸከም የመጡት፣

48 ቍጥራቸው ስምንት ሺሕ ዐምስት መቶ ሰማንያ ነበሩ።

49 እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት እያንዳንዱ በየአገልግሎቱና በየሸክም ሥራው ተደለደለ። ስለዚህም እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ቈጠራቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos