Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘኍል 36 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የሰለጰዓድ ሴት ልጆች ርስት
36፥1-12 ተጓ ምብ – ዘኍ 27፥1-11

1 ከዮሴፍ ዝርያ ጐሣዎች የሆኑ የምናሴ ልጅ፣ የማኪር ልጅ፣ የገለዓድ ጐሣ የቤተ ሰብ አለቆች ወደ ሙሴና የእስራኤላውያን ቤተ ሰቦች አለቆች ወደሆኑት መሪዎች ቀርበው ተናገሩ፤

2 እንዲህም አሉ፤ “ምድሪቱን በዕጣ ከፋፍለህ ለእስራኤላውያን ርስት አድርገህ እንድትሰጣቸው እግዚአብሔር አንተን ጌታዬን ባዘዘ ጊዜ የወንድማችንን የሰለጰዓድን ድርሻ ለሴቶች ልጆቹ እንድትሰጥ አዝዞሃል።

3 ከሌሎች የእስራኤል ነገዶች ባል ቢያገቡ ድርሻቸው ከእኛ የዘር ርስት ላይ ተወስዶ የሚያገቧቸው ሰዎች ላሉበት ነገድ ይተላለፋል፤ ይህ ከሆነ ደግሞ በዕጣ ከተደለደለልን ርስት ላይ ከፊሉ ሊቀነስብን ነው።

4 የእስራኤላውያን ዓመተ ኢዮቤልዩ በሚመጣበት ጊዜ የእነርሱ ድርሻ ወደ ባሎቻቸው ነገድ ይጨመራል፤ ይህ ከሆነም ድርሻቸው ከአባቶቻችን ነገድ ርስት ላይ ይወሰዳል።”

5 ከዚህ በኋላ ሙሴ እግዚአብሔር በተናገረው መሠረት እስራኤላውያንን እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ “የዮሴፍ ነገድ የተናገረው ትክክል ነው፤

6 እንግዲህ የሰለጰዓድን ሴት ልጆች በተመለከተ እግዚአብሔር የሚያዝዘው ይህ ነው፤ ከአባታቸው ነገድ ወገን እስከ ሆነ ድረስ የወደዱትን ማግባት ይችላሉ።

7 እያንዳንዱ እስራኤላዊም ከቀደሙት አባቶቹ በወረሰው ርስት ይጽና፤ በእስራኤል ከአንዱ ነገድ ወደ ሌላው ነገድ የሚተላለፍ ርስት አይኖርም።

8 እያንዳንዱ እስራኤላዊ የየአባቶቹን ርስት መውረስ ስላለበት፣ በማንኛውም የእስራኤል ነገድ ውስጥ ርስት የምትወርስ የትኛዪቱም ሴት፣ ከአባቷ ነገድ ወገን የሆነውን አንዱን ማግባት አለባት።

9 እያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ የወረሰውን መሬት እንዳለ ማቈየት ስላለበት፣ ርስት ከአንዱ ነገድ ወደ ሌላው ነገድ አይተላለፍም።”

10 ስለዚህም የሰለጰዓድ ሴት ልጆች እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ።

11 የሰለጰዓድ ሴት ልጆች፤ ማህለህ፣ ቲርጻ፣ ዔግላ፣ ሚልካ፣ ኑዓ ከአባታቸው ወንድሞች ልጆች ጋራ ተጋቡ።

12 ከዮሴፍ ልጅ ከምናሴ ዝርያ ጐሣዎች ጋራ በመጋባታቸው፣ ርስታቸው በዚያው በአባታቸው ጐሣና ነገድ እጅ እንዳለ ቀረ።

13 ከኢያሪኮ ማዶ፣ በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ፣ በሞዓብ ሜዳ ሳሉ እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ትእዛዞችና ደንቦች እነዚህ ናቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos