Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘኍል 34 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የከነዓን አዋሳኞች

1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤

2 “እስራኤላውያንን እዘዛቸው፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘ርስት አድርጋችሁ በዕጣ ወደምትካፈሏት ወደ ከነዓን ምድር በምትገቡበት ጊዜ አዋሳኞቿ እነዚህ ይሆናሉ፤

3 “ ‘የደቡብ ድንበራችሁ በኤዶም ወሰን ላይ ካለው ከጺን ምድረ በዳ ጥቂቱን ይጨምራል፤ በምሥራቅም በኩል የደቡብ ድንበራችሁ ከጨው ባሕር ጫፍ ይጀምርና

4 በአቅረቢም መተላለፊያ አቋርጦ እስከ ጺን ይሄድና በስተ ደቡብ እስከ ቃዴስ በርኔ ይዘልቃል፤ ከዚያም በሐጸር አዳር ዐልፎ እስከ ዓጽሞን ይደርስና

5 ዞሮ ከግብጽ ወንዝ ደረቅ መደብ ጋራ በመገናኘት መጨረሻው ባሕሩ ይሆናል።

6 የምዕራቡ ድንበራችሁ ደግሞ የታላቁ ባሕር ዳርቻ ይሆናል። በምዕራቡ በኩል ያለው ወሰናችሁም ይኸው ነው።

7 የሰሜን ድንበራችሁን ከታላቁ ባሕር እስከ ሖር ተራራ ምልክት አድርጉበት፤

8 ከሖር ተራራ እስከ ሌቦ ሐማት እንደዚሁ አድርጉ፤ ከዚያም ወሰኑ እስከ ጽዳድ ይሄድና

9 እስከ ዚፍሮን በመቀጠል መጨረሻው ሐጻርዔናን ይሆናል፤ በሰሜን በኩል ያለው ወሰናችሁ ይኸው ነው።

10 ለምሥራቁ ድንበራችሁም እንደዚሁ ከሐጻርዔናን እስከ ሴፋማ ምልክት አድርጉበት።

11 ወሰኑም ከሴፋማ አንሥቶ ከዓይን በስተምሥራቅ እስካለው እስከ ሪብላ ቍልቍል ይወርድና ከኪኔሬት ባሕር በስተምሥራቅ እስካሉት ሸንተረሮች ድረስ ይዘልቃል።

12 ከዚያም ወሰኑ የዮርዳኖስን ወንዝ ተከትሎ መጨረሻው የጨው ባሕር ይሆናል። “ ‘እንግዲህ በዙሪያዋ ካሉት ወሰኖቿ ጋራ ምድራችሁ ይህች ናት።’ ”

13 ሙሴ እስራኤላውያንን እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፤ “ይህችን ምድር ርስት አድርጋችሁ በዕጣ ደልድሉ፤ እግዚአብሔርም ለዘጠኙና ለግማሹ ነገድ እንድትሰጥ አዝዟል፤

14 የሮቤል ነገድ ቤተ ሰቦች፣ የጋድ ነገድ ቤተ ሰቦች እንዲሁም የምናሴ ነገድ እኩሌታ ርስታቸውን ተቀብለዋልና።

15 እነዚህ ሁለቱ ነገዶችና እኩሌታው ነገድ ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ፣ ከኢያሪኮ ማዶ በፀሓይ መውጫ በኩል ርስታቸውን ተቀብለዋል።”

16 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤

17 “ምድሪቱን ርስት አድርገው የሚያከፋፍሏችሁ ካህኑ አልዓዛርና የነዌ ልጅ ኢያሱ ናቸው፤

18 ምድሪቱን በማከፋፈሉ እንዲረዱም ከየነገዱ አንዳንድ መሪ ውሰዱ።

19 “ስማቸውም ይህ ነው፤ “ከይሁዳ ነገድ፣ የዮፎኒ ልጅ ካሌብ፤

20 ከስምዖን ነገድ፣ የዓሚሁድ ልጅ ሰላሚኤል፤

21 ከብንያም ነገድ፣ የኪስሎን ልጅ ኤልዳድ፤

22 የዳን ነገድ መሪ፣ የዩግሊ ልጅ ቡቂ፤

23 የዮሴፍ ልጅ የምናሴ ነገድ መሪ፣ የሱፊድ ልጅ አኒኤል፤

24 የዮሴፍ ልጅ የኤፍሬም ነገድ መሪ፣ የሺፍጣን ልጅ ቀሙኤል፤

25 የዛብሎን ነገድ መሪ፣ የፈርናክ ልጅ ኤሊሳፈን፤

26 የይሳኮር ነገድ መሪ፣ የሖዛ ልጅ ፈልጢኤል፤

27 የአሴር ነገድ መሪ፣ የሴሌሚ ልጅ አሑሒድ፤

28 የንፍታሌም ነገድ መሪ፣ የዓሚሁድ ልጅ ፈዳሄል።”

29 እነዚህ በከነዓን ምድር ለእስራኤላውያን ርስት እንዲያከፋፍሉ እግዚአብሔር ያዘዛቸው ሰዎች ናቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos