Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘኍል 30 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ስእለት

1 ሙሴ ለእስራኤል የነገድ አለቆች እንዲህ አላቸው፤ “እግዚአብሔር ያዘዘው ይህ ነው፤

2 አንድ ሰው ለእግዚአብሔር ስእለት በሚሳልበት ወይም አንድ ነገር ለማድረግ በመሐላ ራሱን ግዴታ ውስጥ በሚያስገባበት ጊዜ ቃሉን ሳያጥፍ ያለውን ሁሉ መፈጸም አለበት።

3 “በአባቷ ቤት የምትኖር ሴት ልጅ ለእግዚአብሔር ስእለት ብትሳል ወይም አንድ ነገር ለማድረግ በመሐላ ራሷን ግዴታ ውስጥ ብታስገባ፣

4 አባቷም መሳሏን ወይም ራሷን ግዴታ ውስጥ ማስገባቷን ሰምቶ ምንም ነገር ሳይላት ቢቀር፣ ስእለቶቿ በሙሉ፣ ራሷንም ግዴታ ውስጥ ያስገባችባቸው ነገሮች ሁሉ መፈጸም ይኖርባቸዋል።

5 አባቷ ይህንኑ ሰምቶ ከከለከላት ግን የትኛውም ስእለቷ ወይም ራሷን ግዴታ ውስጥ ያስገባችበት መሐላ አይያዝባትም፤ የከለከላት አባቷ ስለ ሆነ እግዚአብሔር ነጻ ያደርጋታል።

6 “እንዲሁም ከተሳለች ወይም አምልጧት ተናግራ ራሷን ግዴታ ውስጥ ካስገባች በኋላ ባል ብታገባ፣

7 ባሏም ሰምቶ ምንም ነገር ሳይላት ቢቀር ስእለቶቿ ወይም ራሷን ግዴታ ውስጥ ያስገባችባቸው ነገሮች መፈጸም ይኖርባቸዋል።

8 ሆኖም ባሏ ይህንኑ ሰምቶ ከከለከላት ግን ለመፈጸም የተሳለችውንም ሆነ አምልጧት ተናግራ ራሷን ግዴታ ውስጥ ያስገባችበትን ነገር ስለሚያስቀር እግዚአብሔር ከዚህ ነጻ ያደርጋታል።

9 “ባሏ የሞተባት ወይም ከባሏ የተፋታች ሴት የትኛውም ስእለቷ ወይም የገባችበት ግዴታ ሁሉ የጸና ይሆናል።

10 “ከባሏ ጋራ የምትኖር ሴት ብትሳል ወይም አንድ ነገር ለማድረግ በመሐላ ራሷን ግዴታ ውስጥ ብታስገባና

11 ባሏም ይህንኑ ሰምቶ ምንም ነገር ባይላትና ባይከለክላት ግን ስእለቶቿም ሆኑ ለማድረግ ራሷን ግዴታ ውስጥ ያስገባችባቸው ነገሮች ሁሉ የጸኑ ይሆናሉ።

12 ባሏ ሰምቶ እንዲቀሩ ካደረገ ግን ስእለቶቿንም ሆነ ለማድረግ ቃል የገባቻቸውን ነገሮች የመፈጸም ግዴታ የለባትም፤ ባሏ እንዲቀሩ ስላደረጋቸው እግዚአብሔር ነጻ ያደርጋታል።

13 የትኛውንም ስእለቷን ወይም ራሷን ለመከላከል በመሐላ የታሰረችበትን ሁሉ ባሏ ሊያጸናው ወይም ሊያፈርሰው ይችላል።

14 ይሁን እንጂ ባሏ ግን ስለ ጕዳዩ ከዕለት ወደ ዕለት ምንም ነገር ሳይላት ቢቀር ስእለቶቿን ወይም ራሷን ግዴታ ውስጥ ያስገባችባቸውን ነገሮች ሁሉ እያጸናላት ነው ማለት ነው፤ ስለ ነገሮቹ ሰምቶ ምንም ነገር ሳይላት በመቅረቱ አጽንቶላታል።

15 ስለ ነገሮቹ ከሰማ በኋላ እንዲቀሩ ካደረገ ግን ለፈጸመችው በደል በኀላፊነት የሚጠየቀው ራሱ ነው።”

16 እነዚህ እንግዲህ በባልና በሚስት፣ በአባትና ዐብራው በቤት ውስጥ በምትኖር ልጁ መካከል ያለውን ግንኙነት አስመልክቶ እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠው ሥርዐቶች ናቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos