Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘኍል 24 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም

1 በለዓምም እግዚአብሔር እስራኤልን መባረክ እንደ ወደደ ባየ ጊዜ፣ እንደ ሌላው ጊዜ ሁሉ አስማት ለመሻት አልሄደም፤ ነገር ግን ፊቱን ወደ ምድረ በዳ መለሰ።

2 በለዓም አሻግሮ ተመልክቶ እስራኤል በየነገድ በየነገዱ ሆኖ መስፈሩን ሲያይ የእግዚአብሔር መንፈስ በላዩ መጣበት፤

3 ንግሩንም እንዲህ ሲል ጀመረ፤ “የዚያ ዐይኑ የተከፈተለት፣ የቢዖር ልጅ የበለዓም ንግር፣

4 የዚያ የአምላክን ቃል የሚሰማ፣ ሁሉን ቻይ የአምላክን ራእይ የሚያይ፣ ከመሬት የተደፋው ዐይኖቹም የተከፈቱለት ሰው ንግር፤

5 “ያዕቆብ ሆይ፤ ድንኳኖችህ፣ እስራኤል ሆይ፤ ማደሪያዎችህ እንዴት ያማሩ ናቸው!

6 “እንደ ሸለቆዎች፣ በወንዝ ዳር እንዳሉም የአትክልት ስፍራዎች ተዘርግተዋል፤ በእግዚአብሔር እንደ ተተከሉ አደሶች፣ በውሃም አጠገብ እንዳሉ ዝግባዎች ናቸው።

7 ከማድጋቸው ውሃ ይፈስሳል፤ ዘራቸውም የተትረፈረፈ ውሃ ያገኛል። “ንጉሣቸው ከአጋግ ይልቃል፤ መንግሥታቸውም ከፍ ከፍ ይላል።

8 “እግዚአብሔር ከግብጽ አወጣቸው፤ ብርታታቸውም እንደ ጐሽ ብርታት ነው፤ ጠላቶች የሆኗቸውን ሕዝብ ያነክታሉ፤ ዐጥንቶቻቸውን ያደቅቃሉ፤ በፍላጾቻቸው ይወጓቸዋል።

9 እንደ አንበሳ አድፍጠዋል፤ እንደ እንስቲቱም አንበሳ አድብተዋል፤ ሊቀሰቅሳቸውስ የሚችል ማን ነው? “የሚባርኩህ ቡሩክ፣ የሚረግሙህም ርጉም ይሁኑ።”

10 ከዚያም ባላቅ፣ በበለዓም ላይ እጅግ ተቈጣ፤ እጆቹንም አጨብጭቦ እንዲህ አለው፤ “ጠላቶቼን እንድትረግምልኝ ጠራሁህ፤ አንተ ግን ሦስቱንም ጊዜ ባረክሃቸው።

11 በል ቶሎ ወደ ቤትህ ሂድልኝ፤ ወሮታህን አሳምሬ ልከፍልህ ነበር፤ እግዚአብሔር ግን እንዳታገኝ ከለከለህ።”

12 በለዓምም ለባላቅ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ወደ እኔ ለላክሃቸው ሰዎች እንዲህ ብዬ ነግሬአቸው አልነበረምን?

13 ‘ሌላው ይቅርና ባላቅ በብርና በወርቅ የተሞላ ቤተ መንግሥቱን ቢሰጠኝ እንኳ፣ እግዚአብሔር የሚለውን ብቻ ከመናገር በቀር ከእግዚአብሔር ትእዛዝ ውጭ በራሴ ሐሳብ በጎም ሆነ ክፉ ማድረግ አልችልም።’

14 እንግዲህ ወደ ሕዝቤ እመለሳለሁ፤ ይሁን እንጂ በሚመጣው ዘመን ይህ ሕዝብ በሕዝብህ ላይ የሚያደርገውን ልንገርህ።”


አራተኛው የበለዓም ንግር

15 ከዚያም እንዲህ ሲል ንግሩን ጀመረ፤ “የቢዖር ልጅ የበለዓም ንግር፤ የዚያ ዐይኑ የተከፈተለት ሰው ንግር።

16 የዚያ የአምላክን ቃል የሚሰማ፣ ከልዑልም ዕውቀትን ያገኘው፣ ከሁሉን ቻይ ራእይ የሚገለጥለት፣ መሬት የተደፋው፣ ዐይኖቹም የተገለጡለት ሰው ንግር፤

17 “አየዋለሁ፤ አሁን ግን አይደለም፤ እመለከተዋለሁ፤ በቅርቡ ግን አይደለም፤ ኮከብ ከያዕቆብ ይወጣል፤ በትረ መንግሥት ከእስራኤል ይነሣል። የሞዓብን ግንባሮች፣ የሤትንም ወንዶች ልጆች ራስ ቅል ያደቅቃል።

18 ኤዶም ይሸነፋል፤ ጠላቱ ሴይርም ድል ይሆናል፤ እስራኤል ግን እየበረታ ይሄዳል።

19 ገዥ ከያዕቆብ ይወጣል፤ የተረፉትንም የከተማዪቱን ነዋሪዎች ይደመስሳል።”


የመጨረሻዎቹ የበለዓም ንግሮች

20 ከዚያም በለዓም አማሌቅን አይቶ ንግሩን እንዲህ ሲል ጀመረ፤ “አማሌቅ ከሕዝቦች የመጀመሪያው ነበር፤ በመጨረሻ ግን ይደመሰሳል።”

21 ቄናውያንንም አይቶ ንግሩን እንዲህ ሲል ጀመረ፤ “መኖሪያህ አስተማማኝ ነው፤ ጐጆህም በዐለት ውስጥ ተሠርቷል፤

22 ያም ሆኖ ግን እናንተ ቄናውያን፤ አሦር በምርኮ ሲወስዳችሁ ትደመሰሳላችሁ።”

23 ከዚያም ንግሩን ቀጠለ፤ “ወዮ! አምላክ ይህን ሲያደርግ ማን ይተርፋል?

24 መርከቦች ከኪቲም ዳርቻዎች ይመጣሉ፤ አሦርንና ዔቦርን ይይዛሉ፤ እነርሱም ደግሞ ይደመሰሳሉ።”

25 ከዚህ በኋላ በለዓም ተነሥቶ ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ ባላቅም መንገዱን ቀጠለ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos