ዘኍል 20 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምከዐለት የፈለቀ ውሃ 1 በመጀመሪያው ወር መላው የእስራኤል ማኅበረ ሰብ ወደ ጺን ምድረ በዳ መጥተው በቃዴስ ተቀመጡ፤ እዚያ ማርያም ሞተች፤ ተቀበረችም። 2 በዚህ ጊዜ ለማኅበረ ሰቡ የሚሆን ውሃ አልነበረም፤ ሕዝቡም ሙሴንና አሮንን በመቃወም ተሰበሰቡ። 3 ሙሴን ተጣሉት፤ እንዲህም አሉት፤ “ወንድሞቻችን በእግዚአብሔር ፊት በሞቱ ጊዜ ምነው እኛም ያኔ ሞተን ባረፍነው ኖሮ! 4 የእግዚአብሔርን ማኅበረ ሰብ ወደዚህ ምድረ በዳ ያመጣችሁት ለምንድን ነው! ከነከብቶቻችን እዚሁ እንድናልቅ ነውን? 5 ከግብጽ አውጥታችሁ እህል ወይም በለስ፣ ወይን ወይም ሮማን ወደሌለበት ወደዚህ ክፉ ቦታ ያመጣችሁንስ ለምንድን ነው? የሚጠጣ ውሃ እንኳ ይታጣ!” 6 ሙሴና አሮን ከማኅበረ ሰቡ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሄደው በግንባራቸው ተደፉ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ተገለጠላቸው። 7 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤ 8 “በትሪቱን ውሰድ፤ አንተና ወንድምህ አሮን ማኅበሩን በአንድነት ሰብስቡ፤ እነርሱም እያዩ ዐለቱን ተናገሩት፤ ዐለቱም ውሃ ያወጣል። አንተም ለማኅበረ ሰቡ ከዐለቱ ውሃ ታወጣላቸዋለህ፤ እነርሱና ከብቶቻቸውም ይጠጣሉ።” 9 ስለዚህም ሙሴ ልክ እንደ ታዘዘው በትሩን ከእግዚአብሔር ፊት ወሰደ። 10 እርሱና አሮንም ማኅበሩን በዐለቱ ፊት አንድ ላይ ሰበሰቡ፤ ሙሴም፣ “እናንተ ዐመፀኞች ስሙ፤ ከዚህ ዐለት እኛ ለእናንተ ውሃ ማውጣት አለብን?” አላቸው። 11 ከዚያም ሙሴ እጁን ዘርግቶ በበትሩ ዐለቱን ሁለት ጊዜ መታው፤ ውሃውም ተንዶለዶለ፤ ማኅበረ ሰቡና ከብቶቻቸውም ጠጡ። 12 ነገር ግን እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን፣ “በእስራኤላውያን ፊት እኔን ቅዱስ አድርጋችሁ ለማክበር ስላልታመናችሁብኝ ይህን ማኅበረ ሰብ ወደምሰጠው ምድር ይዛችሁ አትገቡም” አላቸው። 13 እስራኤላውያን ከእግዚአብሔር ጋራ የተጣሉበት፣ እርሱም ቅዱስ መሆኑን በመካከላቸው የገለጠበት ይህ የመሪባ ውሃ ነበር። ኤዶም እስራኤል እንዳያልፍ ከለከለ 14 ሙሴ ከቃዴስ ለኤዶም ንጉሥ እንዲህ ሲል መልእክተኞች ላከ፤ “ወንድምህ እስራኤል የሚለው ይህ ነው፤ የደረሰብን መከራ ሁሉ ምን እንደ ሆነ አንተም ታውቃለህ። 15 የቀድሞ አባቶቻችን ወደ ግብጽ ወረዱ፤ እኛም እዚያ ብዙ ዘመን ኖርን። ግብጻውያን እኛንም አባቶቻችንንም አሠቃዩን፤ 16 ወደ እግዚአብሔር በጮኽን ጊዜ ግን ጩኸታችንን ሰማ፤ መልአክ ልኮም ከግብጽ አወጣን። “አሁንም ያለነው እዚሁ ቃዴስ በግዛትህ ድንበር ላይ ባለችው ከተማ ነው። 17 ስለዚህ በአገርህ እንድናልፍ እባክህን ፍቀድልን፤ በየትኛውም ዕርሻ ወይም የወይን ተክል ውስጥ አንገባም፤ ከየትኛውም ጕድጓድ ውሃ አንጠጣም። የንጉሡን አውራ ጐዳና ይዘን ከመጓዝ በቀር፣ ግዛትህን ዐልፈን እስክንሄድ ድረስ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አንልም።” 18 ኤዶም ግን እንዲህ ሲል መለሰ፤ “በዚህ በኩል አታልፉም፤ እናልፋለን የምትሉ ከሆነ በሰልፍ ወጥተን በሰይፍ እንመታችኋለን።” 19 እስራኤላውያንም መልሰው፣ “አውራውን መንገድ ይዘን እንሄዳለን፤ እኛም ሆንን ከብቶቻችን የትኛውንም ውሃችሁን ከጠጣን ዋጋውን እንከፍላለን፤ በእግር ዐልፈን መሄድ ብቻ እንጂ ሌላ ምንም አንፈልግም።” አሏቸው። 20 ኤዶምም እንደ ገና፣ “በዚህ ማለፍ አትችሉም” የሚል መልስ ሰጣቸው። ከዚያም ኤዶም ብዙና ኀይለኛ የሆነ ሰራዊት አሰልፎ ሊወጋቸው ወጣ፤ 21 ስለዚህ ኤዶም በግዛቱ ዐልፈው እንዳይሄዱ ስለ ከለከላቸው እስራኤላውያን ተመለሱ። የአሮን መሞት 22 መላው የእስራኤል ማኅበረ ሰብ ከቃዴስ ተነሥቶ ወደ ሖር ተራራ መጣ። 23 እግዚአብሔርም በኤዶም ወሰን አጠገብ ባለው በሖር ተራራ ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ 24 “አሮን ወደ ወገኖቹ ይሰበሰባል፤ ሁለታችሁም በመሪባ ውሃ በትእዛዜ ላይ ዐምፃችኋልና ለእስራኤላውያን ወደምሰጣት ምድር አይገባም። 25 አሮንንና ልጁን አልዓዛርን ወደ ሖር ተራራ ይዘሃቸው ውጣ። 26 አሮን ወደ ወገኖቹ ስለሚሰበሰብ ልብሱን አውልቀህ ልጁን አልዓዛርን አልብሰው፤ አሮንም እዚያው ይሞታል።” 27 ሙሴ እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ መላው ማኅበረ ሰብ እያያቸው ወደ ሖር ተራራ ወጡ። 28 ሙሴም የአሮንን ልብስ አውልቆ ልጁን አልዓዛርን አለበሰው፤ አሮንም እዚያው ተራራው ጫፍ ላይ ሞተ። ከዚያም ሙሴና አልዓዛር ከተራራው ወረዱ፤ 29 መላው ማኅበረ ሰብም አሮን መሞቱን በተረዳ ጊዜ፣ የእስራኤል ቤት በሙሉ ሠላሳ ቀን አለቀሰለት። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.