Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘኍል 1 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የሕዝብ ቈጠራ

1 እስራኤላውያን ከግብጽ በወጡ በሁለተኛው ዓመት፣ በሁለተኛው ወር፣ በመጀመሪያው ቀን በሲና ምድረ በዳ ሳሉ እግዚአብሔር ሙሴን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ተናገረው፤ እንዲህም አለው፤

2 “የወንዶቹን ስም አንድ በአንድ በመዘርዘር መላውን የእስራኤል ማኅበረ ሰብ በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው ቍጠሯቸው።

3 በመላው እስራኤል ያሉትን ዕድሜያቸው ሃያና ከዚያም በላይ ሆኖ ለውጊያ ብቁ የሆኑትን ወንዶች ሁሉ አንተና አሮን በየምድባቸው ቍጠሯቸው።

4 ከየነገዱ የአባቶች ቤት ተጠሪ የሆነ አንድ ሰው ከእናንተ ጋራ ይሁን።

5 “የሚረዷችሁም ሰዎች ስም የሚከተለው ነው፤ “ከሮቤል የስዲዮር ልጅ ኤሊሱር፤

6 ከስምዖን የሱሪሰዳይ ልጅ ሰለሚኤል፤

7 ከይሁዳ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን፤

8 ከይሳኮር የሶገር ልጅ ናትናኤል፤

9 ከዛብሎን የኬሎን ልጅ ኤልያብ፤

10 ከዮሴፍ ልጆች ከኤፍሬም የዓሚሁድ ልጅ ኤሊሳማ፤ ከምናሴ የፍዳሱር ልጅ ገማልኤል፤

11 ከብንያም የጋዴዮን ልጅ አቢዳን፤

12 ከዳን የአሚሳዳይ ልጅ አኪዔዘር፤

13 ከአሴር የኤክራን ልጅ ፋግኤል፤

14 ከጋድ የራጉኤል ልጅ ኤሊሳፍ፤

15 ከንፍታሌም የዔናን ልጅ አኪሬ።”

16 እነዚህ ከማኅበረ ሰቡ የተመረጡ የየነገዱ አለቆች ሲሆኑ እነርሱም የእስራኤል ጐሣዎች መሪዎች ነበሩ።

17 ሙሴና አሮን ስማቸው የተጠቀሰውን እነዚህን ሰዎች ወሰዱ፤

18 ከዚያም በሁለተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ማኅበረ ሰቡን በሙሉ በአንድነት ሰበሰቧቸው። የተሰበሰቡትም በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው የትውልድ ሐረጋቸውን ተናገሩ፤

19 እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆነ ወንዶች ስማቸው አንድ በአንድ ተመዘገበ። እንዲህ አድርጎም በሲና ምድረ በዳ ቈጠራቸው።

20 ከእስራኤል የበኵር ልጅ ከሮቤል ዝርያ፦ ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያ በላይ ሆኖ በሰራዊቱ ውስጥ ለማገልገል ብቁ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በየጐሣቸውና፣ በየቤተ ሰባቸው መዝገብ መሠረት ስማቸው አንድ በአንድ ተጻፈ።

21 ከሮቤል ነገድ የተቈጠሩት አርባ ስድስት ሺሕ ዐምስት መቶ ነበሩ።

22 ከስምዖን ዝርያ፦ ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ሆኖ ለመዋጋት ብቁ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው መዝገብ መሠረት ስማቸው አንድ በአንድ ተጻፈ።

23 ከስምዖን ነገድ የተቈጠሩት ዐምሳ ዘጠኝ ሺሕ ሦስት መቶ ነበሩ።

24 ከጋድ ዝርያ፦ ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ሆኖ ለመዋጋት ብቁ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በየጐሣቸውና፣ በየቤተ ሰባቸው መዝገብ መሠረት ስማቸው አንድ በአንድ ተጻፈ።

25 ከጋድ ነገድ የተቈጠሩትም አርባ ዐምስት ሺሕ ስድስት መቶ ዐምሳ ነበሩ።

26 ከይሁዳ ዝርያ፦ ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ሆኖ ለመዋጋት ብቁ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በየጐሣቸውና፣ በየቤተ ሰባቸው መዝገብ መሠረት ስማቸው አንድ በአንድ ተጻፈ።

27 ከይሁዳ ነገድ የተቈጠሩትም ሰባ አራት ሺሕ ስድስት መቶ ነበሩ።

28 ከይሳኮር ዝርያ፦ ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ሆኖ ለመዋጋት ብቁ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በየጐሣቸውና፣ በየቤተ ሰባቸው መዝገብ መሠረት ስማቸው አንድ በአንድ ተጻፈ።

29 ከይሳኮር ነገድ የተቈጠሩትም ዐምሳ አራት ሺሕ አራት መቶ ነበሩ።

30 ከዛብሎን ዝርያ፦ ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ሆኖ ለመዋጋት ብቁ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በየጐሣቸውና፣ በየቤተ ሰባቸው መዝገብ መሠረት ስማቸው አንድ በአንድ ተጻፈ።

31 ከዛብሎን ነገድ የተቈጠሩትም ዐምሳ ሰባት ሺሕ አራት መቶ ነበሩ።

32 ከዮሴፍ ልጆች፦ ከኤፍሬም ዝርያ ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ሆኖ ለመዋጋት ብቁ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው መዝገብ መሠረት ስማቸው አንድ በአንድ ተጻፈ።

33 ከኤፍሬም ነገድ የተቈጠሩትም አርባ ሺሕ ዐምስት መቶ ነበሩ።

34 ከምናሴ ዝርያ፦ ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ሆኖ ለመዋጋት ብቁ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው መዝገብ መሠረት ስማቸው አንድ በአንድ ተጻፈ።

35 ከምናሴ ነገድ የተቈጠሩትም ሠላሳ ሁለት ሺሕ ሁለት መቶ ነበሩ።

36 ከብንያም ዝርያ፦ ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ሆኖ ለመዋጋት ብቁ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በየጐሣቸውና፣ በየቤተ ሰባቸው መዝገብ መሠረት ስማቸው አንድ በአንድ ተጻፈ፤

37 ከብንያም ነገድ የተቈጠሩትም ሠላሳ ዐምስት ሺሕ አራት መቶ ነበሩ።

38 ከዳን ዝርያ፦ ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ሆኖ ለመዋጋት ብቁ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በየጐሣቸውና፣ በየቤተ ሰባቸው መዝገብ መሠረት ስማቸው አንድ በአንድ ተጻፈ።

39 ከዳን ነገድ የተቈጠሩትም ስድሳ ሁለት ሺሕ ሰባት መቶ ነበሩ።

40 ከአሴር ዝርያ፦ ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ሆኖ ለመዋጋት ብቁ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በየጐሣቸውና፣ በየቤተ ሰባቸው መዝገብ መሠረት ስማቸው አንድ በአንድ ተጻፈ።

41 ከአሴር ነገድ የተቈጠሩት አርባ አንድ ሺሕ ዐምስት መቶ ነበሩ።

42 ከንፍታሌም ዝርያ፦ ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ሆኖ ለመዋጋት ብቁ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በየጐሣቸውና፣ በየቤተ ሰባቸው መዝገብ መሠረት ስማቸው አንድ በአንድ ተጻፈ።

43 ከንፍታሌም ነገድ የተቈጠሩትም ዐምሳ ሦስት ሺሕ አራት መቶ ነበሩ።

44 በሙሴና በአሮን፣ እያንዳንዳቸውም ቤተ ሰባቸውን በወከሉት በዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል አለቆች የተቈጠሩት ወንዶች እነዚህ ናቸው።

45 ስለዚህ እስራኤላውያን ሁሉ ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ሆኖ በእስራኤል ሰራዊት ውስጥ ለመዋጋት ብቁ የሆኑት በየቤተ ሰባቸው ተቈጠሩ፤

46 ጠቅላላ ቍጥራቸውም ስድስት መቶ ሦስት ሺሕ ዐምስት መቶ ዐምሳ ነበር።

47 የሌዊ ነገድ ቤተ ሰቦች ግን ከሌሎች ጋራ ዐብረው አልተቈጠሩም፤

48 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎት ነበርና፤

49 “የሌዊን ነገድ አትቍጠር፤ በእስራኤላውያንም ቈጠራ ውስጥ አታስገባው፤

50 በዚህ ፈንታ ሌዋውያንን በምስክሩ ማደሪያ፣ በውስጡ ባሉት በመገልገያ ዕቃዎች ሁሉ እንዲሁም ከዚሁ ጋራ በተያያዙ በማናቸውም ነገሮች ላይ ኀላፊዎች ይሁኑ፤ ማደሪያውንና በውስጡ ያሉትን የመገልገያ ዕቃዎች ይሸከሙ፤ በውስጡ ያገልግሉ፤ ድንኳናቸውንም በዙሪያው ይትከሉ።

51 ማደሪያው በሚነሣበት ጊዜ ሌዋውያን ይንቀሉት፤ ማደሪያው በሚተከልበትም ጊዜ ሌዋውያን ያቁሙት፤ ሌላ ሰው ቢቀርብ ግን ይገደል።

52 እስራኤላውያን በየምድባቸው ድንኳናቸውን ይትከሉ፤ እያንዳንዱም ሰው በየሰፈሩና በየዐርማው ሥር ይስፈር።

53 ሌዋውያን ግን በእስራኤላውያን ማኅበረ ሰብ ላይ ቍጣ እንዳይወርድ ድንኳኖቻቸውን በምስክሩ ማደሪያ ዙሪያ ይትከሉ፤ የምስክሩ ማደሪያ ድንኳን ኀላፊዎች ሌዋውያን ናቸው።”

54 እስራኤላውያንም እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ይህን ሁሉ አደረጉ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos