Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ማቴዎስ 9 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የሽባው ሰው መፈወስ
9፥2-8 ተጓ ምብ – ማር 2፥3-12 ፤ ሉቃ 5፥18-26

1 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ባሕሩን በጀልባ ተሻግሮ ወደ ራሱ ከተማ መጣ።

2 በዚያም ሰዎች አንድ ሽባ ሰው በቃሬዛ ተሸክመው ወደ እርሱ አመጡ። ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን፣ “አይዞህ አንተ ልጅ፤ ኀጢአትህ ተሰርዮልሃል” አለው።

3 በዚህ ጊዜ የአይሁድ ሃይማኖት መምህራን፣ “ይህማ እግዚአብሔርን መሳደብ ነው” በማለት በልባቸው አጕረመረሙ።

4 ኢየሱስ ሐሳባቸውን ተረድቶ እንዲህ አለ፤ “ክፉ ነገር በልባችሁ ለምን ታስባላችሁ?

5 ለመሆኑ፣ ‘ኀጢአትህ ተሰርዮልሃል’ ከማለትና ‘ተነሥተህ ሂድ’ ከማለት የቱ ይቀልላል?

6 ነገር ግን የሰው ልጅ በምድር ላይ ኀጢአትን የማስተስረይ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ ነው” ብሎ፣ ሽባውን፣ “ተነሣ! ቃሬዛህን ይዘህ ወደ ቤትህ ሂድ” አለው።

7 ሽባውም ተነሥቶ ወደ ቤቱ ሄደ።

8 ሕዝቡም ይህን ባዩ ጊዜ ተደነቁ፤ በፍርሀት ተሞልተው፣ እንደዚህ ያለ ሥልጣን ለሰው የሰጠውን እግዚአብሔርን አመሰገኑ።


የማቴዎስ መጠራት
9፥9-13 ተጓ ምብ – ማር 2፥14-17 ፤ ሉቃ 5፥27-32

9 ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ ሲሄድ ማቴዎስ የሚባል አንድ ሰው በቀረጥ መሰብሰቢያው ተቀምጦ አየና፣ “ተከተለኝ” አለው፤ እርሱም ተነሥቶ ተከተለው።

10 ኢየሱስ በማቴዎስ ቤት በማእድ ላይ ሳለ፣ ብዙ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ኀጢአተኞች መጥተው ከእርሱና ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ዐብረው ሊመገቡ ተቀመጡ።

11 ፈሪሳውያንም ይህን ባዩ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን፣ “መምህራችሁ ከቀረጥ ሰብሳቢዎችና ከኀጢአተኞች ጋራ ለምን ዐብሮ ይበላል?” ብለው ጠየቋቸው።

12 ኢየሱስም የተናገሩትን ሰምቶ እንዲህ አላቸው፤ “ሐኪም የሚያስፈልገው ለሕመምተኞች እንጂ ለጤነኞች አይደለም፤

13 ሄዳችሁ፣ ‘ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወድዳለሁ፤’ የሚለውን ቃል ትርጕም አጢኑ፤ ኀጢአተኞችን እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁምና።”


የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ያልጾሙበት ምክንያት
9፥14-17 ተጓ ምብ – ማር 2፥18-22 ፤ ሉቃ 5፥33-39

14 የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ወደ ኢየሱስ ቀርበው፣ “እኛና ፈሪሳውያን ስንጾም፣ የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን ለምን አይጾሙም?” ብለው ጠየቁት።

15 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “ሙሽራው ዐብሯቸው እያለ ዕድምተኞቹ እንዴት ሊያዝኑ ይችላሉ? ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ጊዜ ይመጣል፤ በዚያም ጊዜ ይጾማሉ።

16 “በአሮጌ ልብስ ላይ አዲስ ቍራጭ ጨርቅ የሚጥፍ ሰው የለም፤ ይህ ከሆነ አዲሱ ዕራፊ ካረጀው ልብስ ላይ ተቦጭቆ ቀዳዳውን የባሰ ያሰፋዋል።

17 አዲስ የወይን ጠጅ በአሮጌ አቍማዳ ማንም አያስቀምጥም፤ ይህ ከሆነ አቍማዳው ይፈነዳል፤ የወይን ጠጁም ይፈስሳል፤ አቍማዳውም ከጥቅም ውጭ ይሆናል። ነገር ግን አዲስ የወይን ጠጅ በአዲስ አቍማዳ ይጨመራል፤ በዚህ ሁኔታ የወይን ጠጁና አቍማዳው በደኅና ተጠብቀው ይቈያሉ።”


ከሞት የተነሣችው ልጅና ከደም መፍሰስ የተፈወሰችው ሴት
9፥18-26 ተጓ ምብ – ማር 5፥22-43 ፤ ሉቃ 8፥41-56

18 ኢየሱስ ሰዎቹን በማናገር ላይ ሳለ፣ አንድ የምኵራብ አለቃ መጥቶ ከፊቱ ተደፍቶ፣ “ልጄ አሁን ሞተችብኝ፤ በሕይወት እንድትኖር መጥተህ እጅህን ጫንባት” አለው።

19 ኢየሱስም ተነሥቶ ዐብሮት ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት።

20 ከዚያም ዐሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈስሳት የኖረች አንዲት ሴት ከበስተኋላው ተጠግታ የልብሱን ጫፍ ነካች።

21 እርሷም በልቧ፣ “የልብሱን ጫፍ እንኳ ብነካ እፈወሳለሁ” ብላ ነበር።

22 ኢየሱስም ወደ ኋላ ዘወር ብሎ ሴቲቱን አያትና፣ “አይዞሽ፣ ልጄ ሆይ፤ እምነትሽ አድኖሻል” አላት። ሴቲቱም ወዲያውኑ ተፈወሰች።

23 ኢየሱስ ወደ ሹሙ ቤት እንደ ደረሰ እንቢልተኞችንና የሚንጫጫውን ሕዝብ አይቶ፣

24 “ዞር በሉ፤ ብላቴናዪቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” አላቸው፤ እነርሱ ግን ሣቁበት።

25 ሕዝቡም ከወጣ በኋላ ወደ ውስጥ ገብቶ እጇን ያዘ፤ ብላቴናዪቱም ተነሥታ ቆመች።

26 ወሬውም በአካባቢው ሁሉ ተሠራጨ።


የዐይነ ስውሮቹና የድዳው መፈወስ

27 ኢየሱስም ከዚያ እንደ ሄደ ሁለት ዐይነ ስውሮች፣ “የዳዊት ልጅ፤ ማረን!” በማለት እየጮኹ ተከተሉት።

28 ዐይነ ስውሮቹም ኢየሱስ ወደ ገባበት ቤት ተከትለው ገቡ፤ ኢየሱስም፣ “ዐይናችሁን ላበራላችሁ እንደምችል ታምናላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “አዎን፣ ጌታ ሆይ፤” ብለው መለሱለት።

29 ከዚያም ኢየሱስ ዐይኖቻቸውን ዳስሶ፣ “እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ” አላቸው።

30 ዐይኖቻቸውም በሩ፤ ኢየሱስም፣ “ይህን ማንም እንዳያውቅ” ብሎ በጥብቅ አስጠነቀቃቸው።

31 እነርሱ ግን ወጥተው በአካባቢው ሁሉ ስለ ኢየሱስ አወሩ።

32 ከዚያም ሲወጡ፣ በጋኔን የተያዘ ድዳ ሰው ወደ እርሱ አመጡ።

33 ጋኔኑ ከወጣለት በኋላ ድዳው መናገር ጀመረ፤ ሕዝቡም ተደንቀው፣ “እንዲህ ያለ ነገር በእስራኤል ምድር ታይቶ አያውቅም” አሉ።

34 ፈሪሳውያን ግን፣ “አጋንንትን የሚያወጣው፣ በአጋንንት አለቃ ነው” አሉ።


ሠራተኞች ጥቂቶች ናቸው

35 ኢየሱስ በምኵራቦቻቸው እያስተማረ፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች ቃል እየሰበከ፣ እንዲሁም ደዌንና ሕመምን ሁሉ እየፈወሰ በከተሞቹና በመንደሮቹ ዞረ።

36 ሕዝቡም እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተጨንቀውና ተመልካች የለሽ ሆነው ባየ ጊዜ ዐዘነላቸው።

37 ደቀ መዛሙርቱንም እንዲህ አላቸው፤ “መከሩ ብዙ ነው፤ ሠራተኞቹ ግን ጥቂቶች ናቸው፤

38 ስለዚህ የመከሩ ጌታ፣ ሠራተኞችን ወደ መከሩ እንዲልክ ለምኑት።”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos