ኢያሱ 21 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምለሌዋውያን የተመደቡ ከተሞች 21፥4-39 ተጓ ምብ – 1ዜና 6፥54-80 1 የሌዋውያን ቤተ ሰብ አለቆች ወደ ካህኑ ወደ አልዓዛር፣ ወደ ነዌ ልጅ ወደ ኢያሱና ወደ ሌሎቹ የእስራኤል ነገድ አባቶች ዘንድ ቀረቡ፤ 2 በከነዓን ምድር በሴሎም፣ “እግዚአብሔር የምንኖርባቸውን ከተሞች፣ ከብቶቻችን ከሚሰማሩባቸው ቦታዎች እንድትሰጡን በሙሴ በኩል አዝዞልን ነበር” አላቸው። 3 ስለዚህ እስራኤላውያን ከወረሱት ምድር ላይ የሚከተሉትን ከተሞችና መሰማሪያዎች እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ለሌዋውያኑ ሰጡ። 4 የመጀመሪያው ዕጣ ለቀዓት ዘሮች በየጐሣቸው ወጣ፤ የካህኑ የአሮን ዝርያዎች ለሆኑት ሌዋውያን ከይሁዳ፣ ከስምዖንና ከብንያም ነገዶች ዐሥራ ሦስት ከተሞች በዕጣ ተመደቡላቸው። 5 ለቀሩት ለቀዓት ዘሮች ደግሞ ከኤፍሬምና ከዳን ነገድ ጐሣዎች፣ እንዲሁም ከምናሴ ነገድ እኩሌታ ጐሣዎች ዐሥር ከተሞች በዕጣ ተመደቡላቸው። 6 ለጌርሶን ዝርያዎች ከይሳኮር፣ ከአሴር፣ ከንፍታሌም ነገድ ጐሣዎችና ባሳን ውስጥ ካለው ከምናሴ ነገድ እኩሌታ ጐሣዎች ዐሥራ ሦስት ከተሞች ተመደቡላቸው። 7 ለሜራሪ ዝርያዎች በየጐሣቸው ከሮቤል፣ ከጋድና ከዛብሎን ነገዶች ዐሥር ከተሞች ተመደቡላቸው። 8 ስለዚህ እስራኤላውያን እግዚአብሔር በሙሴ በኩል ባዘዘው መሠረት፣ እነዚህን ከተሞችና መሰማሪያቸውን ለሌዋውያኑ በዕጣ መደቡላቸው። 9 ከይሁዳና ከስምዖን ነገዶች ደግሞ ከዚህ በታች በስም የተጠቀሱትን ከተሞች በዕጣ መደቡላቸው። 10 እነዚህም ከተሞች የሌዊ ልጆች፣ የቀዓት ጐሣዎች ለሆኑት ለአሮን ዝርያዎች ተመደቡ፤ ይህም የሆነው የመጀመሪያው ዕጣ ለእነርሱ ስለ ወጣላቸው ነበር፤ 11 እነርሱም በተራራማው የይሁዳ ምድር ያለችውን ኬብሮን የተባለችውን ቂርያት አርባቅን በዙሪያዋ ካለው መሰማሪያ ጋራ ሰጧቸው፤ አርባቅ የዔናቅ አባት ነበረ። 12 ይሁን እንጂ በከተማዪቱ ዙሪያ ያሉትን ዕርሻዎችና መንደሮች ለዮፎኒ ልጅ ለካሌብ ርስት አድርገው ሰጡት። 13 እንደዚሁም ለነፍሰ ገዳይ የመማፀኛ ከተማ የሆነችውን ኬብሮንንና ልብናን ከነመሰማሪያቸው ለካህኑ ለአሮን ልጆች ሰጧቸው፤ 14 ደግሞም የቲርን፣ ኤሽትሞዓን፣ 15 ሖሎንን፣ ዳቤርን፣ 16 ዓይንን፣ ዩጣንና ቤትሳሚስን ከነመሰማሪያቸው ሰጧቸው፤ እነዚህ ዘጠኙ ከተሞች ከሁሉ ነገዶች ይዞታ ላይ ተከፍለው የተሰጡ ናቸው። 17 ከብንያም ነገድ፣ ገባዖን፣ ጌባዕ፣ 18 ዓናቶትና አልሞን የተባሉትን አራት ከተሞች ከነመሰማሪያዎቻቸው ሰጧቸው። 19 ለካህናቱ ለአሮን ዝርያዎች ከነመሰማሪያቸው የተሰጧቸው ከተሞች ዐሥራ ሦስት ነበሩ። 20 የሌዊ ልጅ የቀዓት ጐሣዎች ለሆኑት ለሌሎቹ ደግሞ ከኤፍሬም ነገድ ላይ ተከፍለው የሚከተሉት ከተሞች በዕጣ ተመደቡላቸው። 21 በተራራማው በኤፍሬም አገርም ለነፍሰ ገዳይ መማፀኛ የሆነችው ሴኬምና ጌዝር፣ 22 ቂብጻይሞና ቤትሖሮን ከነመሰማሪያዎቻቸው አራት ከተሞች ተሰጧቸው። 23 እንዲሁም ከዳን ነገድ፣ ኤልተቄን፣ ገባቶን፤ 24 ኤሎንና ጋትሪሞን ከነመሰማሪያዎቻቸው አራት ከተሞች ተሰጧቸው። 25 ከምናሴ ነገድ፣ እኩሌታ ደግሞ ታዕናክና ጋትሪሞን ከነመሰማሪያዎቻቸው ሁለት ከተሞች ተሰጧቸው። 26 እነዚህ ዐሥር ከተሞች ሁሉ ከነመሰማሪያዎቻቸው ለተቀሩት የቀዓት ጐሣዎች ተሰጧቸው። 27 የጌርሶን ወገኖች ለሆኑት ለሌሎቹ የሌዊ ጐሣዎች የተሰጧቸው የሚከተሉት ናቸው፤ ከምናሴ ነገድ እኩሌታ፣ በባሳን ውስጥ ለነፍሰ ገዳይ መማፀኛ የሆነችው ከተማ ጎላንና በኤሽትራ እነዚህ ሁለት ከተሞች ከነመሰማሪያዎቻቸው፤ 28 ከይሳኮር ነገድ፣ ቂሶን፣ ዳብራት፣ 29 የርሙትና ዓይንገኒም፣ እነዚህ አራት ከተሞች ከነመሰማሪያዎቻቸው፤ 30 ከአሴር ነገድ፣ ሚሽአል፣ ዓብዶን፣ 31 ሔልቃትና ረአብ እነዚህ አራት ከተሞች ከነመሰማሪያዎቻቸው፤ 32 ከንፍታሌም ነገድ፣ በገሊላ ውስጥ ለነፍሰ ገዳይ መማፀኛ የሆነችው ከተማ ቃዴስ፣ ሐሞትዶርና ቀርታን እነዚህ ሦስት ከተሞች ከነመሰማሪያዎቻቸው፤ 33 ለጌርሶናውያን ጐሣዎች የተመደቡት ከተሞች ሁሉ ከነመሰማሪያዎቻቸው ዐሥራ ሦስት ነበሩ። 34 የሜራሪ ጐሣዎች ለሆኑት ለተቀሩት ሌዋውያን የተሰጧቸው የሚከተሉት ናቸው፤ ከዛብሎን ነገድ፣ ዮቅንዓም፣ ቀርታ፣ 35 ዲሞናና ነህላል፣ እነዚህ አራት ከተሞች ከነመሰማሪያዎቻቸው፤ 36 ከሮቤል ነገድ፣ ቦሶር፣ ያሀጽ፣ 37 ቅዴሞትና ሜፍዓት፣ እነዚህ አራት ከተሞች ከነመሰማሪያዎቻቸው፤ 38 ከጋድ ነገድ፣ በገለዓድ ውስጥ ለነፍሰ ገዳይ መማፀኛ የሆነችው ከተማ ራሞት መሃናይም፣ 39 ሐሴቦንና ኢያዜር፣ እነዚህ አራት ከተሞች ከነመሰማሪያዎቻቸው። 40 የሜራሪ ጐሣዎች ለሆኑት ለተቀሩት ሌዋውያን የተመደቡት ከተሞች ሁሉ ዐሥራ ሁለት ነበሩ። 41 እንግዲህ እስራኤላውያን ርስት አድርገው ከያዙት ምድር ለሌዋውያኑ የተሰጧቸው ከተሞች ከነመሰማሪያዎቻቸው በአጠቃላይ አርባ ስምንት ነበሩ። 42 እነዚህም ከተሞች እያንዳንዳቸው በዙሪያቸው መሰማሪያዎች ነበሯቸው፤ መሰማሪያ የሌለው ከተማ አልነበረም። 43 ስለዚህ እግዚአብሔር ለቀድሞ አባቶቻቸው ይሰጣቸው ዘንድ የማለላቸውን ምድር ሁሉ ለእስራኤል ሰጠ፤ እነርሱም ምድሪቱን ወረሱ፣ መኖሪያቸውም አደረጓት። 44 እግዚአብሔር ለቀድሞ አባቶቻቸው እንደ ማለላቸው በዙሪያቸው ካሉት አሳረፋቸው፤ አንድም ጠላት ሊቋቋማቸው አልቻለም፤ እግዚአብሔር ጠላቶቻቸውን ሁሉ አሳልፎ በእጃቸው ሰጥቷቸዋልና። 45 እግዚአብሔር ለእስራኤል ቤት ከሰጠው መልካም የተስፋ ቃል አንዳችም አልቀረም፤ ሁሉም ተፈጽሟል። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.