Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኢያሱ 20 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የመማፀኛ ከተሞች
20፥1-9 ተጓ ምብ – ዘኍ 35፥9-34 ፤ ዘዳ 4፥41-43 ፤ 19፥1-14

1 ከዚያም እግዚአብሔር ኢያሱን እንዲህ አለው፤

2 “በሙሴ በኩል በነገርኋችሁ መሠረት የመማፀኛ ከተሞች እንዲለዩ ለእስራኤላውያን ንገራቸው፤

3 ሳያስበው ድንገት ሰው የገደለ ማንኛውም ሰው ወደዚያ በመሸሽ ከደም ተበቃዩ እንዲያመልጥ ከተማዪቱ መጠለያ ትሁን።

4 ገዳዩ ከነዚህ ከተሞች ወደ አንዲቱ በሚሸሽበት ጊዜ፣ በከተማዪቱ መግቢያ በር ላይ ቆሞ ጕዳዩን ለከተማዪቱ ሽማግሌዎች ይንገራቸው፤ ከዚያም እነርሱ ወደ ከተማቸው አስገብተው የሚኖርበትን ስፍራ ሰጥተውት ዐብሯቸው ይቀመጥ።

5 ደም ተበቃዩ ተከታትሎት ቢመጣ፣ ሆነ ብሎና በክፋት ተነሣሥቶ ወንድሙን የገደለው ባለመሆኑ፣ ሰዎቹ ነፍሰ ገዳዩን አሳልፈው አይስጡት።

6 በማኅበሩ ፊት ለፍርድ እስኪቀርብና በዚያ ጊዜ የሚያገለግለው ሊቀ ካህናት እስኪሞት ድረስ በዚያች ከተማ ይቈይ። ከዚያም ወደ ቤቱ፣ ሸሽቶ ወደ መጣበት ከተማ ሊመለስ ይችላል።”

7 ስለዚህም በኰረብታማው በንፍታሌም ምድር በገሊላ ቃዴስን፣ በኰረብታማው በኤፍሬም ምድር ሴኬምን፣ በኰረብታማው በይሁዳ ምድር ኬብሮን የምትባለውን ቂርያት አርባቅን ለዩ።

8 እንደዚሁም ከዮርዳኖስ ማዶ ከኢያሪኮ በስተምሥራቅ በሮቤል ነገድ ይዞታ ውስጥ ከፍታ ባለው ምድረ በዳ ያለችውን ቦሶርን፣ በጋድ ነገድ ይዞታ ውስጥ ባለችው በገለዓድ የምትገኘውን ራሞትንና በምናሴ ነገድ ይዞታ ውስጥ በባሳን የምትገኘውን ጎላንን ለዩ።

9 ሳያስበው በድንገት ሰው የገደለ ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም በመካከላቸው የሚኖር ማንኛውም መጻተኛ ወደ ተለዩት ከተሞች መሸሽ ይችላል፤ በማኅበሩ ፊት ከመቆሙ አስቀድሞም በደም ተበቃዩ መገደል የለበትም።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos