Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኢያሱ 17 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም

1 ምናሴ የዮሴፍ የበኵር ልጅ እንደ መሆኑ መጠን፣ ለነገዱ የተመደበለት ድርሻ ይህ ነበር፤ የምናሴ የበኵር ልጅ ማኪር፣ የገለዓዳውያን አባት ብርቱ ጦረኛ ስለ ነበር ገለዓድና ባሳን ድርሻው ሆኑ።

2 ስለዚህ ይህ ርስት ለተቀሩት የምናሴ ዘሮች ማለትም ለአቢዔዝር፣ ለኬሌግ፣ ለአሥሪኤል፣ ለሴኬም፣ ለአፌር፣ ለሸሚዳ ጐሣዎች የተሰጠ ነው፤ እነዚህ በየጐሣዎቻቸው የዮሴፍ ልጅ የምናሴ ሌሎች ወንዶች ዝርያዎች ናቸው።

3 ሰለጰዓድ የአፌር ልጅ፣ የገለዓድ ልጅ፣ የማኪር ልጅ፣ የምናሴ ልጅ ነው። እርሱም ሴቶች ልጆች እንጂ ወንዶች ልጆች አልነበሩትም። የሴቶች ልጆቹም ስም ማህለህ፣ ኑዓ፣ ዔግላ፣ ሚልካ፣ ቲርጻ ይባላል።

4 እነርሱም ወደ ካህኑ ወደ አልዓዛር፣ ወደ ነዌ ልጅ ወደ ኢያሱና ወደ መሪዎቹ ቀርበው፣ “ከወንድሞቻችን ጋራ ርስት እንድንካፈል እግዚአብሔር ሙሴን አዝዞታል” አሏቸው። ስለዚህ ኢያሱ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት፣ ከአባታቸው ወንድሞች ጋራ ርስት ሰጣቸው።

5 ምናሴም ከገለዓድና ከባሳን ምድር ሌላ፣ ዐሥር ቦታ የሚደለደል የመሬት ክፍል በዮርዳኖስ ምሥራቅ ነበረው፤

6 የምናሴ ነገድ ሴት ልጆች ከወንዶቹ ጋራ ርስት ተካፍለዋልና። የገለዓድ ምድር ግን ለቀሩት የምናሴ ዘሮች ተሰጠ።

7 የምናሴ ርስት ከአሴር አንሥቶ ከሴኬም በስተምሥራቅ እስካለችው እስከ ሚክምታት ይደርሳል፤ ድንበሩም ወደ ደቡብ በመዝለቅ በዓይንታጱዋ የሚኖረውን ሕዝብ ይጨምራል።

8 የታጱዋ ምድር የምናሴ ይዞታ ነበር፤ ይሁን እንጂ በድንበሩ ላይ የምትገኘው የታጱዋ ከተማ የኤፍሬም ዘሮች ይዞታ ነበረች።

9 ከዚያም በመቀጠል ድንበሩ በደቡብ በኩል ወደ ቃና ወንዝ ይደርሳል። በምናሴ ከተሞችም መካከል የኤፍሬም ከተሞች ነበሩ፤ ያም ሆኖ የምናሴ ድንበር የወንዙ ሰሜናዊ ክፍል ሲሆን፣ እስከ ባሕሩ ይዘልቃል።

10 በደቡብ በኩል ያለው ምድር የኤፍሬም ሲሆን፣ በሰሜን በኩል ያለው ደግሞ የምናሴ ነበር፤ የምናሴ ግዛት እስከ ባሕሩ የሚደርስ ሲሆን፣ ሰሜናዊ ድንበሩ አሴር፣ ምሥራቃዊ ድንበሩ ደግሞ ይሳኮር ነው።

11 እንዲሁም በይሳኮርና በአሴር ውስጥ ቤትሳን፣ ይብለዓም፣ የዶር ሕዝብ፣ ዓይንዶር፣ ታዕናክና መጊዶ በዙሪያቸው ካሉ ሰፈሮቻቸው ጋራ የምናሴ ነበሩ፤ ሦስተኛውም ናፎት ነው።

12 ይሁን እንጂ የምናሴ ዘሮች እነዚህን ከተሞች መያዝ አልቻሉም፤ ከነዓናውያን የያዙትን ላለመልቀቅ ቍርጥ ሐሳብ አድርገው ነበርና።

13 እስራኤላውያን በበረቱ ጊዜ ግን ከነዓናውያንን የጕልበት ሥራ እንዲሠሩ አስገደዷቸው እንጂ ከዚያ ፈጽመው አላባረሯቸውም ነበር።

14 የዮሴፍ ዘሮች ኢያሱን፣ “ቍጥራችን ብዙ ነው፤ እግዚአብሔርም አብዝቶ ባርኮናል፤ ታዲያ እንዴት ርስታችን አንድ ዕጣና አንድ ድርሻ ብቻ ሆነ?” አሉት።

15 ኢያሱም መልሶ፣ “ቍጥራችሁ ይህን ያህል በዝቶ ኰረብታማው የኤፍሬም ምድር እስከዚህ የሚጠብባችሁ ከሆነ፣ ወደ ፌርዛውያንና ወደ ራፋይም ምድር ወጥታችሁ ደኑን ለራሳችሁ መንጥሩ” አላቸው።

16 የዮሴፍም ዘሮች፣ “ኰረብታማው አገር አይበቃንም፤ ደግሞም በሜዳው ላይ ያሉት በቤትሳንና በሰፈሮቿ፣ እንዲሁም በኢይዝራኤል ሸለቆ የሚኖሩት ከነዓናውያን ሁሉ የብረት ሠረገሎች አሏቸው” አሉት።

17 ኢያሱ ግን ለዮሴፍ ዘሮች ለኤፍሬምና ለምናሴ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ ቍጥራችሁ ብዙ፣ እጅግም ኀያል እንደ መሆናችሁ ድርሻችሁ አንድ ብቻ አይሆንም፤

18 ነገር ግን ደን የለበሰው ኰረብታማው አገር የእናንተ ነው፤ ሄዳችሁ መንጥሩት፣ ዳር ድንበሩ ሁሉ የእናንተ ይሆናል፤ ከነዓናውያን የብረት ሠረገላ ቢኖራቸውና ብርቱዎች ቢሆኑም እንኳ ከዚያ ታስወጧቸዋላችሁ።”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos