Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኢያሱ 16 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ለኤፍሬምና ለምናሴ ነገድ የተመደበው ድርሻ

1 ለዮሴፍ ዝርያዎች የተመደበው ድርሻ፣ ከዮርዳኖስ ኢያሪኮ፣ ማለት ከኢያሪኮ ምንጮች በስተምሥራቅ ይነሣና፣ ምድረ በዳውን በማቋረጥ በኰረብታማው አገር አድርጎ ወደ ቤቴል ይወጣል።

2 ሎዛ ከምትባለው ከቤቴል ይነሣና በአጣሮት ወደሚገኘው ወደ አርካውያን ግዛት ይሻገራል፣

3 በዚያም በምዕራብ በኩል ቍልቍል ወደ የፍሌጣውያን ግዛት እስከ ታችኛው ቤትሖሮን ምድር ይወርድና ወደ ጌዝር ዘልቆ ባሕሩ ላይ ይቆማል።

4 ስለዚህ የዮሴፍ ዘሮች ምናሴና ኤፍሬም ርስታቸውን ተቀበሉ።

5 ለኤፍሬም ወገን በየጐሣ በየጐሣቸው የተሰጣቸው ድርሻ ይህ ነው፤ ድንበሩ በምሥራቅ በኩል ከአጣሮት አዳር ተነሥቶ እስከ ላይኛው ቤትሖሮን ይወጣና፣

6 እስከ ባሕሩ ይዘልቃል። በስተሰሜን ደግሞ ከሚክምታት ተነሥቶ በምሥራቅ በኩል ወደ ተአናት ሴሎ ይታጠፍና ከዚያ በማለፍ እስከ ኢያኖክ ምሥራቅ ይዘልቃል።

7 ከኢያኖክም በመነሣት ወደ አጣሮትና ወደ ነዓራት ቍልቍል ይወርድና በኢያሪኮ በኩል አድርጎ ዮርዳኖስ ላይ ብቅ ይላል።

8 ድንበሩ አሁንም ከታጱዋ በምዕራብ በኩል አድርጎ ወደ ቃና ወንዝ ይወርድና ከባሕሩ ላይ ይቆማል። እንግዲህ የኤፍሬም ነገድ በየጐሣ በየጐሣቸው የተካፈሉት ርስት ይህ ነበር።

9 ይህም በምናሴ ነገድ ርስት ውስጥ ለኤፍሬም ዘሮች የተመደቡትን ከተሞች በሙሉና መንደሮቻቸውን የሚያጠቃልል ነው።

10 ይህ ሁሉ ሆኖ የኤፍሬም ዘሮች በጌዝር የሚኖሩትን ከነዓናውያን ከዚያ አላባረሯቸውም ነበር፤ ከነዓናውያን እስከ ዛሬ ድረስ ከኤፍሬም ዘሮች ጋራ ዐብረው ይኖራሉ፤ ይሁን እንጂ የጕልበት ሥራ እንዲሠሩ ይገደዳሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos