Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኢያሱ 14 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ ስላለው ምድር አከፋፈል

1 ካህኑ አልዓዛር፣ የነዌ ልጅ ኢያሱና የእስራኤል የየነገዱ ጐሣ አባቶች የደለደሉላቸው፣ እስራኤላውያንም በከነዓን ምድር የወረሱት ርስት ይህ ነው።

2 ርስታቸውም እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት፣ ለዘጠኙ ነገድና ለእኩሌታው ነገድ በዕጣ ተከፋፈለ።

3 ሙሴ ለሁለቱ ነገድና ለእኩሌታው፣ የዮርዳኖስን ምሥራቅ ክፍል ርስት አድርጎ ሰጣቸው፤ ሌዋውያኑ ግን ዐብረዋቸው እንዲካፈሉ አላደረገም፤

4 የዮሴፍ ልጆች ምናሴና ኤፍሬም ሁለት ነገዶች ሆነው ነበርና፤ ለሌዋውያኑ ግን ከሚኖሩባቸው ከተሞች እንዲሁም ለበግ፣ ለፍየልና ለከብት መንጎቻቸው መሰማሪያ እንዲሆን ዐብሮ የተከለለላቸውን ምድር ብቻ እንጂ ሌላ አልሰጣቸውም።

5 ስለዚህ እስራኤላውያን እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት፣ ምድሪቱን ተካፈሉ።


ኬብሮን ለካሌብ ተሰጠች

6 የይሁዳም ሰዎች በጌልገላ ወደ ኢያሱ ቀረቡ፤ ከዚያም የቄኔዛዊው የዮፎኒ ልጅ ካሌብ እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር በቃዴስ በርኔ ስለ አንተና ስለ እኔ፣ የእግዚአብሔር ሰው ለሆነው ለሙሴ የተናገረውን ታውቃለህ።

7 የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ምድሪቱን እንድሰልል ከቃዴስ በርኔ በላከኝ ጊዜ የአርባ ዓመት ሰው ነበርሁ፤ እኔም ትክክለኛውን ማስረጃ ይዤለት መጣሁ፤

8 ዐብረውኝ ወደዚያ የወጡት ወንድሞቼ ግን፣ የሕዝቡ ልብ በፍርሀት እንዲቀልጥ አደረጉ፤ ሆኖም እኔ አምላኬን እግዚአብሔርን በፍጹም ልቤ ተከተልሁት።

9 ስለዚህም ሙሴ በዚያች ዕለት፣ ‘አምላኬን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ ተከትለኸዋልና እግርህ የረገጣት ምድር ለዘላለም የአንተና የዘርህ ርስት ትሆናለች’ ብሎ ማለልኝ።

10 “አሁንም እነሆ፤ ልክ እግዚአብሔር እንዳለው ይህን ለሙሴ ከተናገረበት ጊዜ አንሥቶ እስራኤል በምድረ በዳ ሲንከራተት እኔን አርባ ዐምስት ዓመት በሕይወት ጠብቆ አኑሮኛል፤ ይኸው ዛሬ ሰማንያ ዐምስት ዓመት ሆነኝ።

11 ሙሴ በላከኝ ጊዜ የነበረኝ ብርታት ዛሬም ዐብሮኝ አለ፤ ልክ እንደዚያን ጊዜ ሁሉ አሁንም ወደ ጦርነት ለመሄድ፣ ለመውጣትም ለመግባትም ኀይሉም ብርታቱም አለኝ።

12 አሁንም እግዚአብሔር በዚያች ዕለት ቃል የገባልኝን ይህችን ኰረብታማ አገር ሰጠኝ። ዔናቃውያን በዚያ እንደ ነበሩና ከተሞቻቸውም ታላላቅና የተመሸጉ እንደ ሆኑ ያን ጊዜ አንተው ራስህ ሰምተሃል፤ ሆኖም ልክ እርሱ እንዳለው በእግዚአብሔር ርዳታ አሳድጄ አወጣቸዋለሁ።”

13 ከዚያም ኢያሱ የዮፎኒን ልጅ ካሌብን ባረከው፤ ኬብሮንንም ርስት አድርጎ ሰጠው።

14 ስለዚህም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ኬብሮን የቄኔዛዊው የዮፎኒ ልጅ የካሌብ ርስት ሆነች፤ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን በፍጹም ልቡ ተከትሏልና።

15 ኬብሮን ቀድሞ ከዔናቃውያን ሁሉ ታላቅ በሆነው ሰው በአርባቅ ስም ቂርያት አርባቅ ተብላ ትጠራ ነበር። ከዚያም ምድሪቱ ከጦርነት ዐረፈች።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos