Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኢያሱ 13 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ወደ ፊት የሚያዝ ምድር

1 ኢያሱ በሸመገለና ዕድሜው በገፋ ጊዜ፣ እግዚአብሔር እንዲህ አለው፤ “እነሆ አርጅተሃል፤ ዕድሜህም ገፍቷል፤ ነገር ግን መያዝ ያለበት እጅግ በጣም ሰፊ ምድር ገና አለ።

2 “የሚቀረውም ምድር ይህ ነው፤ “እርሱም የፍልስጥኤማውያንና የጌሹራውያን አገር ሁሉ ነው፤

3 ከግብጽ በስተምሥራቅ ከሚገኘው ከሺሖር ወንዝ አንሥቶ፣ በሰሜን እስከ አቃሮን ወሰን ያለው አገር፣ ሁሉም እንደ ከነዓናውያን ምድር ይቈጠራል። ይኸውም በጋዛ፣ በአሽዶድ፣ በአስቀሎና፣ በጋትና በአቃሮን የሚኖሩትን የዐምስቱን የፍልስጥኤማውያን ገዦች ምድር የሚያካትት ሲሆን፣ ይህም የኤዋውያን ምድር ነበር።

4 በደቡብ በኩል፤ የከነዓናውያን ምድር ሁሉና የሲዶናውያን ይዞታ ከሆነችው ከመዓራ አንሥቶ እስከ አፌቅ ያለው የአሞራውያን ግዛት፣

5 የጌባላውያንም ምድር፤ በምሥራቅም ከበኣልጋድ አንሥቶ በአርሞንዔም ተራራ ግርጌ ዐልፎ፣ እስከ ሐማት መተላለፊያ ያለው የሊባኖስ ምድር ሁሉ ነው።

6 “ከሊባኖስ እስከ ማስሮን ባለው ተራራማ ምድር ላይ የሚኖሩትን ሁሉ፣ ሲዶናውያንንም ጭምር እኔው ራሴ ከእስራኤላውያን ፊት አሳድጄ አስወጣቸዋለሁ። ብቻ አንተ ባዘዝሁህ መሠረት ምድሪቱን ርስት አድርገህ ለእስራኤላውያን አካፍል።

7 ይህንም ለዘጠኙ ነገድና ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ርስት አድርገህ አካፍል።”


ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ ያለው ምድር አከፋፈል

8 ሌላው የምናሴ ነገድ እኩሌታ፣ የሮቤል ነገድና የጋድ ነገድ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ እንደየድርሻቸው ከፋፍሎ በመደበላቸው መሠረት፣ ራሱ ሙሴ የሰጣቸውን ርስት ተቀበሉ።

9 ይህም ከአርኖን ሸለቆ ዳርቻ ካለው ከአሮዔርና በሸለቆው መካከል ካለችው ከተማ አንሥቶ እስከ ዲቦን የሚደርሰውን የሜድባን ደጋማ ምድር በሙሉ ይይዛል፤

10 እንዲሁም በሐሴቦን ተቀምጦ እስከ አሞናውያን ዳርቻ የገዛውን የአሞራውያንን ንጉሥ የሴዎንን ከተሞች ሁሉ ያጠቃልላል።

11 በተጨማሪም ገለዓድን፣ የጌሹራውያንንና የማዕካታውያንን ግዛት ሁሉ፣ የአርሞንዔምን ተራራ በሙሉ፣ ባሳንንም ሁሉ እስከ ሰልካ ድረስ ይይዛል።

12 ይህም በአስታሮትና በኤድራይ ሆኖ የገዛውን በባሳን ያለውን የዐግን መንግሥት በሙሉ ያጠቃልላል፤ ዐግም በሕይወት ከቀሩት ከመጨረሻዎቹ ከራፋይም ዘሮች አንዱ ነበር። እነዚህንም ሙሴ ድል አደረጋቸው፤ ምድራቸውንም ያዘ፤

13 ነገር ግን እስራኤላውያን የጌሹርንና የማዕካትን ሕዝብ ስላላስወጡ፣ እስከ ዛሬ ድረስ በመካከላቸው ይኖራሉ።

14 ለሌዊ ነገድ ግን ርስት አልሰጠም፤ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርበው ቍርባን በተሰጣቸው ተስፋ መሠረት ርስታቸው ነውና።

15 ሙሴ በየጐሣቸው መድቦ ለሮቤል ነገድ የሰጠው ርስት ይህ ነው፤

16 ድንበራቸው ከአርኖን ሸለቆ ዳርቻ ካለው ከአሮዔርና ከሸለቆው መካከል ካለችው ከተማ አንሥቶ ያለው ግዛት ሲሆን፣ ሜድባ አጠገብ ያለውን ደጋውን አገር በሙሉ፣

17 ሐሴቦንና በደጋው ላይ ያሉትን ከተሞቿን በሙሉ፣ እንዲሁም ዲቦንን፣ ባሞትባኣልን፣ ቤትበኣልምዖን፣

18 ያሀጽን፣ ቅዴሞትን፣ ሜፍዓትን፣

19 ቂርያታይምን፣ ሴባማን፣ በሸለቆው ኰረብታ ላይ ያለችውን ጼሬትሻሐርን፣

20 ቤተ ፌጎርን፣ የፈስጋን ሸንተረሮችና ቤትየሺሞትን፣

21 ማለት በደጋው አገር የሚገኙት ከተሞች ሁሉና መቀመጫውን በሐሴቦን አድርጎ የገዛውን የአሞራውያንን ንጉሥ የሴዎንን ግዛት በሙሉ ያካትታል። ሙሴ ሴዎንንና በዚያው ምድር ተቀማጭ የነበሩትን መሳፍንት፤ ኤዊ፣ ሮቆም፣ ሱር፣ ሑርና ሪባ የተባሉትን የምድያም አለቆች ድል አደረጋቸው።

22 በጦር ሜዳ ከሞቱት ሌላ እስራኤላውያን የቢዖርን ልጅ ሟርተኛውን በለዓምን በሰይፍ መትተው ገደሉት።

23 የሮቤል ነገድ ወሰን የዮርዳኖስ ወንዝ ነው። የሮቤል ነገድ በየጐሣቸው የወረሷቸው ከተሞችና መንደሮቻቸው እነዚህ ነበሩ፤

24 ሙሴ በየጐሣቸው መድቦ ለጋድ ነገድ የሰጠው ርስት ይህ ነው፤

25 ድንበራቸው ኢያዜር፣ የገለዓድን ከተሞች በሙሉ በረባት አጠገብ እስካለው እስከ አሮዔር የሚደርሰውን የአሞናውያን አገር እኩሌታ፣

26 ከሐሴቦን እስከ ራማት ምጽጳና ከዚያም እስከ ብጦኒም፣ ከመሃናይም እስከ ደቤር ግዛት ያለውን፣

27 በሸለቆው ውስጥ ደግሞ ቤትሀራምን፣ ቤትኒምራን፣ ሱኮትን፣ ዳፎንንና እስከ ኪኔሬት ባሕር ጫፍ የሚደርሰውን ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ ያለውን ቀሪውን የሐሴቦን ንጉሥ የሴዎንን ግዛት ያካትታል።

28 የጋድ ነገድ በየጐሣቸው የወረሷቸው ከተሞችና መንደሮቻቸው እነዚህ ነበሩ።

29 ሙሴ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ማለት ለገሚሱ የምናሴ ቤተ ሰብ ዘሮች በየጐሣቸው የሰጣቸው ርስት ይህ ነው፤

30 ድንበራቸው ከመሃናይም አንሥቶ ባሳንን በሙሉ ይጨምርና፣ በባሳን ያሉትን ስድሳ የኢያዕር ከተሞች ሁሉ ይዞ የባሳን ንጉሥ የዐግን ግዛት ሁሉ የሚያካትት ሲሆን፣

31 የገለዓድን እኩሌታ፣ በባሳን የዐግ መንግሥት ዋና ከተማ የሆኑትን አስታሮትንና ኤድራይን ይጨምራል። እነዚህ ለምናሴ ልጅ ለማኪር ዘሮች የተሰጡ ሲሆን፣ ይህም ለግማሾቹ የማኪር ልጆች በየጐሣቸው የተሰጡ ናቸው።

32 ሙሴ ከኢያሪኮ በስተምሥራቅ፣ ከዮርዳኖስ ማዶ በሞዓብ ሜዳ ሳለ የሰጣቸው ርስት ይህ ነበር።

33 ለሌዊ ነገድ ግን ሙሴ ርስት አልሰጠም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንደ ተናገራቸው እርሱ ራሱ ርስታቸው ነውና።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos