Biblia Todo Logo
La Biblia Online

- Anuncios -


ዘዳግም 3 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የባሳን ንጉሥ የዐግ መሸነፍ

1 ከዚያም ተመልሰን ወደ ባሳን የሚወስደውን መንገድ ይዘን ወጣን፤ የባሳን ንጉሥ ዐግም ከመላው ሰራዊቱ ጋራ ሆኖ በኤድራይ ጦርነት ሊገጥመን ተነሣ።

2 እግዚአብሔር፣ “እርሱን፣ መላው ሰራዊቱንና ምድሩን በእጅህ አሳልፌ ስለ ሰጠሁህ፣ አትፍራው፤ ሐሴቦንን ይገዛ በነበረው በአሞራውያን ንጉሥ በሴዎን ላይ ያደረግህበትን በርሱም ላይ አድርግበት” አለኝ።

3 ስለዚህ አምላካችን እግዚአብሔር የባሳንን ንጉሥ ዐግን ከመላው ሰራዊቱ ጋራ ሁሉ እንደዚሁ በእጃችን ላይ ጣላቸው፤ እኛም አንድ እንኳ በሕይወት ሳናስቀር አጠፋናቸው።

4 በዚያ ጊዜ ከተሞቹን ሁሉ ያዝን፤ የዐግ ግዛት ከሆነው፣ በባሳን ከሚገኘው ከጠቅላላው የአርጎብ ክልል ስድሳ ከተሞች ውስጥ፣ እኛ ያልያዝነው አንድም ከተማ አልነበረም።

5 እነዚህ ከተሞች ሁሉ ከፍ ባሉ ቅጥሮች፣ በመዝጊያዎችና በመወርወሪያዎች የተመሸጉ ነበሩ፤ እንዲሁም ቅጥር የሌላቸው አያሌ መንደሮች ነበሩ።

6 በእያንዳንዱ ከተማ ያሉትን ወንዶቹን፣ ሴቶቹንና ልጆቻቸውን ጭምር በማጥፋት፣ በሐሴቦን ንጉሥ በሴዎን ላይ እንዳደረግነው ሁሉ፣ እነዚህንም ፈጽመን ደመሰስናቸው።

7 ከብቱን በሙሉና ከየከተሞቻቸው የማረክነውን ሁሉ ግን ለራሳችን አደረግን።

8 ስለዚህ በዚያ ጊዜ ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ የሚገኘውን፣ ከአርኖን ሸለቆ እስከ አርሞንዔም ተራራ ያለውን ግዛት፣ ከእነዚህ ከሁለቱ የአሞራውያን ነገሥታት ላይ ወሰድንባቸው።

9 አርሞንዔምን፣ ሲዶናውያን ሢርዮን ብለው ሲጠሩት፣ አሞራውያን ግን ሳኔር ይሉታል።

10 በከፍታው ቦታ ላይ የሚገኙትን ከተሞች በሙሉ፣ ገለዓድን እንዳለ፣ እስከ ሰልካና እስከ ኤድራይ ያለውን ባሳንን ሁሉ እንዲሁም በባሳን ውስጥ የሚገኙትን የዐግ ግዛት ከተሞች በእጃችን አደረግን።

11 ከራፋይማውያን ወገን የተረፈ የባሳን ንጉሥ ዐግ ብቻ ነበር። ዐልጋው ከብረት የተሠራ ቁመቱም ዘጠኝ ክንድ፣ ስፋቱ ደግሞ አራት ክንድ ነበር። ይህም እስካሁን በአሞናውያን ከተማ በረባት ይገኛል።


እስራኤላውያን ምድሪቱን መከፋፈላቸው

12 በዚያ ጊዜ ከያዝነው ምድር ላይ በአርኖን ሸለቆ አጠገብ ካለችው ከአሮዔር አንሥቶ በስተሰሜን ያለውን ግዛት፣ በተጨማሪም ኰረብታማውን የገለዓድ አገር እኩሌታ ከነከተሞቹ ለሮቤላውያንና ለጋዳውያን ሰጠኋቸው።

13 ቀሪውን የገለዓድ ምድርና የዐግ ግዛት የሆነውን ባሳንን በሙሉ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ሰጠሁ። በባሳን የሚገኘው መላው የአርጎብ ክልል የራፋይማውያን ምድር በመባል ይታወቅ ነበር።

14 ከምናሴ ነገድ የሆነው ኢያዕር፣ እስከ ጌሹራውያንና እስከ ማዕካታውያን ወሰን ድረስ የሚገኘውን መላውን የአርጎብ ምድር ወሰደ፤ ምድሪቱም በስሙ ተጠራች፤ ከዚሁ የተነሣ ባሳን እስከ ዛሬ ድረስ ሓቦት ኢያዕር ትባላለች።

15 ገለዓድንም ለማኪር ሰጠሁት።

16 ነገር ግን የሸለቆውን እኩሌታ ወሰን በማድረግ ከገለዓድ አንሥቶ እስከ አርኖን ሸለቆ፣ ከዚያም የአሞናውያን ድንበር እስከ ሆነው እስከ ያቦቅ ወንዝ ያለውን ግዛት ለሮቤላውያንና ለጋዳውያን ሰጠኋቸው።

17 የምዕራቡ ወሰን፣ በዓረባ የሚገኘው ዮርዳኖስ ሲሆን፣ ይኸውም ከፈስጋ ተረተሮች በታች፣ ከኪኔሬት አንሥቶ የጨው ባሕር እስከሚባለው እስከ ዓረባ ባሕር ድረስ ነው።

18 በዚያ ጊዜ እኔ እንዲህ ብዬ አዘዝኋችሁ፤ “አምላካችሁ እግዚአብሔር ይህችን ምድር ርስት አድርጎ ለእናንተ ሰጥቷችኋል፤ ይሁን እንጂ የአካል ብቃት ያላቸው ሰዎቻችሁ ሁሉ ለጦርነት ዝግጁ ሆነው ከወንድሞቻችሁ ከእስራኤላውያን ፊት በመቅደም መሻገር አለባቸው።

19 ሆኖም ሚስቶቻችሁና ልጆቻችሁ፣ (ብዙ ከብቶች እንዳሏችሁም ስለማውቅ) ከብቶቻችሁም በሰጠኋችሁ ከተሞች ውስጥ ይቈዩ፤

20 ይኸውም፣ እግዚአብሔር ለእናንተ እንዳደረገው ሁሉ ወንድሞቻችሁን እስኪያሳርፋቸውና አምላካችሁ እግዚአብሔር ከዮርዳኖስ ማዶ የሚሰጣቸውን ምድር እነርሱም እንደዚሁ እስኪወርሱ ድረስ ነው፤ ከዚያ በኋላ እያንዳንዳችሁ ወደ ሰጠኋችሁ ርስት ትመለሳላችሁ።”


ሙሴ ዮርዳኖስን እንዳይሻገር መከልከሉ

21 በዚያ ጊዜ ኢያሱን እንዲህ ስል አዘዝሁት፤ “አምላካችሁ እግዚአብሔር በእነዚህ በሁለቱ ነገሥታት ላይ ያደረገውን ሁሉ በገዛ ዐይንህ አይተሃል፤ አሁንም ዐልፈህ በምትሄድባቸው መንግሥታት ላይ ሁሉ እግዚአብሔር ይህንኑ ይደግመዋል።

22 አምላካችሁ እግዚአብሔር ራሱ ይዋጋላችኋልና አትፍሯቸው።”

23 በዚያ ጊዜ እግዚአብሔርን እንዲህ ብዬ ለመንሁት፤

24 “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ታላቅነትህንና ብርቱ ክንድህን ለእኔ ለባሪያህ እነሆ ማሳየት ጀምረሃል፤ ለመሆኑ በሰማይም ሆነ በምድር፣ አንተ የምታደርጋቸውን ሥራዎችና ታላላቅ ድርጊቶች መፈጸም የሚችል አምላክ ማነው?

25 አሁንም ከዮርዳኖስ ማዶ ያለችውን ያችን መልካሚቱን ምድር፣ ውብ የሆነችውን ኰረብታማ አገርና ሊባኖስን እንዳይ ፍቀድልኝ።”

26 እግዚአብሔር ግን በእናንተ ሰበብ ተቈጥቶኝ ነበርና አልሰማኝም፤ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ “ይበቃል፤ ከእንግዲህ ወዲያ ስለዚህ ነገር አታንሣብኝ።

27 ወደ ፈስጋ ተራራ ጫፍ ውጣ፤ ወደ ምዕራብና ወደ ሰሜን፣ ወደ ደቡብና ወደ ምሥራቅም ተመልከት። አንተ ዮርዳኖስን ስለማትሻገር፣ ምድሪቱን በዐይንህ ብቻ እያት።

28 ነገር ግን ሕዝቡን መርቶ በማሻገር የምታያትን ምድር እንዲወርሱ የሚያደርጋቸው ስለ ሆነ፣ ኢያሱን ላከው፤ አደፋፍረው፤ አበረታታውም።”

29 ስለዚህ እኛ በቤተ ፌጎር አጠገብ ባለው ሸለቆ ውስጥ ቈየን።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos