Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


2 ነገሥት 2 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ኤልያስ ወደ ሰማይ ዐረገ

1 እግዚአብሔር ኤልያስን በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ የሚወስድበት ጊዜ ሲደርስ፣ ኤልያስና ኤልሳዕ ከጌልገላ ተነሥተው ይጓዙ ነበር።

2 ኤልያስም ኤልሳዕን፣ “እግዚአብሔር እኔን ወደ ቤቴል ልኮኛልና አንተ በዚሁ ቈይ” አለው። ኤልሳዕ ግን፣ “ሕያው እግዚአብሔርን፣ በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፤ ከአንተ አልለይም” አለው። ስለዚህ ዐብረው ወደ ቤቴል ወረዱ።

3 በቤቴል የነበሩ የነቢያት ማኅበር ወደ ኤልሳዕ ወጥተው፣ “እግዚአብሔር፣ ጌታህን ኤልያስን ዛሬ ከአንተ ነጥሎ እንደሚወስደው ዐውቀሃልን?” አሉት። ኤልሳዕም፣ “አዎን ዐውቄአለሁ፤ እናንተ ግን ዝም በሉ” አለ።

4 ከዚያም ኤልያስ፣ “ኤልሳዕ ሆይ፤ እግዚአብሔር እኔን ወደ ኢያሪኮ ልኮኛልና አንተ በዚሁ ቈይ” አለው። እርሱም፤ “ሕያው እግዚአብሔርን፣ በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፤ ከአንተ አልለይም” ሲል መለሰ። ስለዚህ ዐብረው ወደ ኢያሪኮ ሄዱ።

5 በኢያሪኮ የነበሩትም የነቢያት ማኅበር ወደ ኤልሳዕ ወጥተው፣ “ለመሆኑ እግዚአብሔር፣ ጌታህን ኤልያስን ዛሬ ከአንተ ነጥሎ እንደሚወስደው ዐውቀሃልን?” አሉት። እርሱም፣ “አዎን ዐውቄአለሁ፤ እናንተ ግን ዝም በሉ” ሲል መለሰ።

6 ከዚያም ኤልያስ፣ “እግዚአብሔር እኔን ወደ ዮርዳኖስ ልኮኛልና አንተ እዚሁ ቈይ” አለው። እርሱም፣ “ሕያው እግዚአብሔርን፤ በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፤ ከአንተ አልለይም” ሲል መለሰ። ስለዚህ ሁለቱም ዐብረው ሄዱ።

7 ከነቢያትም ማኅበር ዐምሳው ሄደው፣ ኤልያስና ኤልሳዕ ከቆሙበት ከዮርዳኖስ ትይዩ ራቅ ብለው ቆሙ።

8 ኤልያስም ካባውን አውልቆ ጠቀለለውና ውሃውን መታበት፤ ከዚያም ውሃው ግራና ቀኝ ተከፈለ፤ ሁለቱም በደረቅ ምድር ተሻገሩ።

9 ከተሻገሩ በኋላም ኤልያስ ኤልሳዕን፤ “ከአንተ ከመወሰዴ በፊት ምን ላደርግልህ እንደምትፈልግ ንገረኝ” አለው። ኤልሳዕም፣ “መንፈስህ በዕጥፍ እንዲያድርብኝ እለምንሃለሁ” ብሎ መለሰ።

10 ኤልያስም፣ “አስቸጋሪ ነገር ጠይቀሃል፤ ይሁን እንጂ እኔ ከአንተ ስወሰድ ብታየኝ፣ እንዳልከው ይሆንልሃል፤ አለዚያ ግን አይሆንም” አለው።

11 እያዘገሙም ሲነጋገሩ ሳለ፣ የእሳት ሠረገላና የእሳት ፈረሶች ድንገት በመካከላቸው ገብተው ሁለቱን ለዩአቸው፤ ኤልያስም በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ዐረገ።

12 ኤልሳዕም ይህን አይቶ፣ “አባቴ አባቴ የእስራኤል ሠረገሎችና ፈረሰኞች!” ብሎ ጮኸ፤ ዳግመኛም ኤልያስን አላየውም፤ ከዚያም የገዛ ልብሱን ይዞ ከሁለት ቦታ ቀደደው።

13 እርሱም ከኤልያስ የወደቀውን ካባ አነሣ፤ ተመልሶም በዮርዳኖስ ወንዝ ዳር ቆመ።

14 ከኤልያስ፣ የወደቀውንም ካባ ይዞ ውሃውን መታና፣ “የኤልያስ አምላክ እግዚአብሔር ወዴት ነው?” አለ። ውሃውን ሲመታውም ውሃው በግራና በቀኝ ተከፈለ፤ ኤልሳዕም ተሻገረ።

15 ከኢያሪኮም መጥተው ይህን ያዩ የነበሩት የነቢያት ወገኖች፣ “የኤልያስ መንፈስ በኤልሳዕ ላይ ዐርፏል” አሉ፤ ሊያገኙትም ሄደው በፊቱ ወደ መሬት ዝቅ ብለው እጅ ነሡ።

16 ከዚያም፣ “እነሆ፤ እኛ አገልጋዮችህ እዚህ ዐምሳ ጠንካራ ሰዎች አሉን፤ ምናልባትም የእግዚአብሔር መንፈስ ጌታህን አንሥቶ ከአንዱ ተራራ ላይ አስቀምጦት ወይም ከአንዱ ሸለቆ አግብቶት ይሆናልና እስኪ ሄደው ይፈልጉት” አሉት። ኤልሳዕም፣ “አይሆንም፤ አትላኳቸው” አለ።

17 አይሆንም ለማለት ዕፍረት እስኪሰማው ድረስ ግድ አሉት፤ ስለዚህ፣ “በሉ እንግዲያው ላኳቸው” አለ። እነርሱም ዐምሳ ሰዎች ላኩ፤ ሰዎቹም ሦስት ቀን ሙሉ ፈልገው ሳያገኙት ቀሩ።

18 በኢያሪኮ ቈይቶ ወደ ነበረው ወደ ኤልሳዕ በተመለሱም ጊዜ፣ “ቀድሞውንስ ቢሆን አትሂዱ ብያችሁ አልነበረምን?” አላቸው።


የውሃው መፈወስ

19 የከተማዪቱም ሰዎች ኤልሳዕን፣ “እነሆ ጌታችን፤ እንደምታያት ይህች ከተማ ለኑሮ የተመቸች ናት፤ ይሁን እንጂ ውሃው መጥፎ ሲሆን ምድሪቱም ፍሬ የማትሰጥ ናት” አሉት።

20 እርሱም፣ “እስኪ በአዲስ ማሰሮ ጨው ጨምራችሁ አምጡልኝ” አለ፤ እንዳለውም አመጡለት።

21 ከዚያም ወደ ውሃው ምንጭ ሄዶ ጨው ጣለበትና “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ይህን ውሃ ፈውሼዋለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲያ ለሞት ምክንያት አይሆንም፤ ምድሪቱንም ፍሬ እንዳትሰጥ አያደርጋትም’ አለ።”

22 ኤልሳዕ እንደ ተናገረውም ውሃው እስከ ዛሬ ድረስ የተፈወሰ ነው።


በኤልሳዕ ላይ ተፌዘበት

23 ኤልሳዕም ከዚያ ተነሥቶ ወደ ቤቴል ወጣ፤ በመንገድ ላይ ሲሄድ ሳለም ልጆች ከከተማ ወጥተው፣ “አንተ መላጣ፤ ውጣ! አንተ መላጣ ውጣ!” እያሉ አፌዙበት።

24 ኤልሳዕም ዘወር ብሎ ተመለከታቸውና በእግዚአብሔር ስም ረገማቸው፤ ከዚያም ሁለት እንስት ድቦች ከዱር ወጥተው ከልጆቹ አርባ ሁለቱን ሰባበሯቸው።

25 እርሱም ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ሄደ፤ ከዚያም ወደ ሰማርያ ተመለሰ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos