Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


2 ዜና መዋዕል 30 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ሕዝቅያስ ፋሲካን ማክበሩ

1 ሕዝቅያስ የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ፋሲካ ለማክበር በኢየሩሳሌም ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንዲመጡ፣ ለመላው እስራኤልና ለይሁዳ መልእክት ላከ፤ ለኤፍሬምና ለምናሴም ደብዳቤ ጻፈ።

2 ንጉሡ፣ ሹማምቱና መላው የኢየሩሳሌም ጉባኤ የፋሲካውን በዓል በሁለተኛው ወር ለማክበር ተስማሙ።

3 በቂ ካህናት ራሳቸውን ስላልቀደሱና ሕዝቡም ገና በኢየሩሳሌም ስላልተሰበሰቡ፣ በዓሉን በወቅቱ ለማክበር አልቻሉም ነበር።

4 ንጉሡና መላው ጉባኤም ዕቅዱ ትክክል ሆኖ አገኙት።

5 ስለዚህ የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ፋሲካ ለማክበር ሕዝቡ ከመላው ኢየሩሳሌም እንዲመጣ፣ ከቤርሳቤህ እስከ ዳን ድረስ ዐዋጅ እንዲነገር ወሰኑ፤ በተጻፈው መሠረት በዓሉ ብዛት ባለው ሕዝብ ተከብሮ አያውቅም ነበርና።

6 መልእክተኞችም በንጉሡ ትእዛዝ፣ የንጉሡንና የሹማምቱን ደብዳቤ ይዘው ወደ እስራኤልና ወደ ይሁዳ ሁሉ ሄዱ፤ ደብዳቤውም እንዲህ የሚል ነበር፤ “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ፤ እርሱ ወደ ተረፋችሁት፣ ከአሦር ነገሥታትም እጅ ወዳመለጣችሁት፣ ወደ እናንተ እንዲመለስ እናንተም የአብርሃም፣ የይሥሐቅና የእስራኤል አምላክ ወደ ሆነው ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ።

7 እንደምታዩት ሁሉ መሣለቂያ እስኪያደርጋቸው ድረስ፣ ለአባቶቻቸው አምላክ ለእግዚአብሔር እንዳልታመኑ እንደ አባቶቻችሁና እንደ ወንድሞቻችሁ አትሁኑ።

8 እንደ አባቶቻችሁም ዐንገተ ደንዳኖች አትሁኑ፤ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ እርሱ ለዘላለም ወደ ቀደሰውም መቅደስ ኑ። አስፈሪ ቍጣው ከእናንተ እንዲመለስም፣ እግዚአብሔር አምላካችሁን አገልግሉ።

9 እናንተ ወደ እግዚአብሔር ብትመለሱ፣ አምላካችሁ እግዚአብሔር ቸርና ርኅሩኅ ስለ ሆነ ወንድሞቻችሁና ልጆቻችሁን በማረኳቸው ዘንድ ምሕረትን ያገኛሉ፤ ወደዚህች ምድር ይመለሳሉ። እናንተ ወደ እርሱ ብትመለሱ፣ እርሱም ፊቱን ከእናንተ አይመልስም።”

10 መልእክተኞቹም በኤፍሬምና በምናሴ ምድር ከአንዱ ከተማ ወደ ሌላው ከተማ በመዘዋወር እስከ ዛብሎን ድረስ ሄዱ፤ ሕዝቡ ግን አንቋሸሻቸው፤ ተሣለቀባቸውም።

11 ሆኖም ከአሴር፣ ከምናሴና ከዛብሎን ጥቂት ሰዎች ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።

12 እንዲሁም ንጉሡና ሹማምቱ በእግዚአብሔር ቃል መሠረት ያዘዙትን እንዲፈጽሙ አንድ ልብ ይሰጣቸው ዘንድ የእግዚአብሔር እጅ በይሁዳ ላይ ነበር።

13 በሁለተኛው ወር የቂጣን በዓል ለማክበር እጅግ ብዙ ሕዝብ በኢየሩሳሌም ተሰበሰበ።

14 በኢየሩሳሌም የነበሩትን መሠዊያዎች ነቃቅለው፣ የዕጣን መሠዊያዎችንም ከስፍራው አንሥተው ወደ ቄድሮን ሸለቆ ጣሉ።

15 በሁለተኛው ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካውን በግ ዐረዱ። ካህናቱና ሌዋውያኑ ዐፍረው ስለ ነበር ራሳቸውን ቀደሱ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትንም ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አመጡ።

16 ከዚያም በእግዚአብሔር ሰው በሙሴ ሕግ እንደ ታዘዘው መደበኛ ቦታቸውን ያዙ። ካህናቱም ከሌዋውያኑ እጅ የተቀበሉትን ደም ረጩ።

17 ከጉባኤው መካከል አብዛኛዎቹ ራሳቸውን ያልቀደሱ ስለ ነበሩ፣ ሌዋውያኑ በሥርዐቱ መሠረት ራሳቸውን ላላነጹትና ጠቦቶቻቸውን ለእግዚአብሔር መቀደስ ላልቻሉት ሁሉ የፋሲካውን በጎች ማረድ ነበረባቸው።

18 ምንም እንኳ ከኤፍሬም፣ ከምናሴ፣ ከይሳኮርና ከዛብሎን ከመጡት አብዛኛዎቹ ራሳቸውን ያላነጹ ቢሆንም ከተጻፈው ትእዛዝ ውጭ ፋሲካውን በሉ። ሕዝቅያስ ግን እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “ቸሩ እግዚአብሔር ሆይ፤ ይቅር በላቸው፤

19 ምንም እንኳ በመቅደሱ ሥርዐት መሠረት የነጹ ሆነው ባይገኙም፣ የአባቶቻቸው አምላክ የሆነውን እግዚአብሔር አምላካቸውን ለመፈለግ ልባቸውን የሚያዘጋጁትን ሁሉ ይቅር በላቸው።”

20 እግዚአብሔርም ሕዝቅያስን ሰማው፤ ሕዝቡንም ፈወሰ።

21 ሌዋውያኑና ካህናቱ በእግዚአብሔር የዜማ ዕቃ ታጅበው፣ በየዕለቱ ለእግዚአብሔር እየዘመሩ፣ በኢየሩሳሌም የነበሩት እስራኤላውያን የቂጣን በዓል በታላቅ ደስታ ለሰባት ቀን አከበሩ።

22 ሕዝቅያስም በእግዚአብሔር አገልግሎት አስተዋዮች የነበሩትን ሌዋውያን ሁሉ በንግግሩ አበረታታ። በሰባቱም የቀን በዓል ቀናት እየበሉና የኅብረት መሥዋዕቱንም እያቀረቡ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገኑ።

23 ጉባኤውም ሁሉ በተከታዩ ሰባት ቀን በዓሉን እንደ ገና ለማክበር ተስማሙ፣ ስለዚህ በዓሉን ለሰባት ተጨማሪ ቀን በታላቅ ደስታ አከበሩ።

24 የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ አንድ ሺሕ ወይፈን፣ ሰባት ሺሕ በግና ፍየል ለጉባኤው ሰጠ፤ ሹማምቱም እንደዚሁ አንድ ሺሕ ወይፈን፣ ዐሥር ሺሕ በግና ፍየል ሰጡ። እጅግ ብዙ ካህናትም ራሳቸውን ቀደሱ።

25 መላው የይሁዳ ጉባኤ፣ ካህናቱና ሌዋውያኑ፣ ከእስራኤል የተሰበሰበው ጉባኤ ሁሉ፣ እንዲሁም ከእስራኤል የመጡ መጻተኞችና በይሁዳ የሚኖሩ መጻተኞች ደስ አላቸው።

26 ከእስራኤል ንጉሥ ከዳዊት ልጅ ከሰሎሞን ጊዜ አንሥቶ በኢየሩሳሌም እንዲህ ያለ በዓል ተደርጎ ስለማያውቅ፣ በኢየሩሳሌም ታላቅ ደስታ ሆነ።

27 ከዚያም ካህናቱና ሌዋውያኑ ተነሥተው ሕዝቡን ባረኩ፤ እግዚአብሔርም ሰማቸው፤ ጸሎታቸውም ወደ ሰማይ ወደ ቅዱሱ ማደሪያው ደረሰ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos