1 ሳሙኤል 4 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም1 የሳሙኤልም ቃል ወደ እስራኤል ሁሉ ደረሰ። በዚያ ዘመን እስራኤላውያን ፍልስጥኤማውያንን ሊወጉ ወጡ፤ እስራኤላውያን በአቤንኤዘር፣ ፍልስጥኤማውያን ደግሞ በአፌቅ ሰፈሩ። ታቦቱ በፍልስጥኤማውያን ተማረከ 2 ፍልስጥኤማውያን እስራኤልን ለመግጠም ሰራዊታቸውን አሰለፉ፤ ጦርነቱ እንደ ተፋፋመም፣ እስራኤላውያን በፍልስጥኤማውያን ተሸነፉ፤ በጦርነቱም ላይ አራት ሺሕ ያህል እስራኤላውያን ተገደሉ። 3 ሰራዊቱ ወደ ሰፈር በተመለሰ ጊዜ የእስራኤል አለቆች፣ “ዛሬ እግዚአብሔር በፍልስጥኤማውያን እንድንሸነፍ ያደረገን ለምንድን ነው? ዐብሮን እንዲወጣ፣ ከጠላቶቻችንም እጅ እንዲያድነን የእግዚአብሔርን የኪዳኑን ታቦት ከሴሎ እናምጣ” አሉ። 4 ስለዚህ ሕዝቡ ሰዎችን ወደ ሴሎ ልከው፣ በኪሩቤል መካከል በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውን የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔርን የኪዳን ታቦት አስመጡ፤ ሁለቱ የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ከእግዚአብሔር የኪዳኑ ታቦት ጋራ በዚያ ነበሩ። 5 የእግዚአብሔር የኪዳኑ ታቦት ወደ ሰፈር በገባ ጊዜ፣ ምድሪቱ እስክትናወጥ ድረስ እስራኤላውያን ሁሉ ታላቅ የደስታ ጩኸት አሰሙ። 6 ፍልስጥኤማውያንም ይህን ታላቅ ጩኸት ሲሰሙ፣ “በዕብራውያን ሰፈር የምንሰማው ይህ ሁሉ ጩኸት ምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁ። የእግዚአብሔር ታቦት ወደ ሰፈር መምጣቱን በተረዱ ጊዜ፤ 7 ፍልስጥኤማውያንም ፈርተው እንዲህ አሉ፤ “አምላክ ወደ ሰፈሩ መጥቷል፤ ወዮልን! እንዲህ ዐይነት ነገር ገጥሞን አያውቅም። 8 ወዮልን! ከእነዚህ ኀያላን አማልክት እጅ ማን ያድነናል? ግብጻውያንን በምድረ በዳ በልዩ ልዩ መቅሠፍት የመቱ እነዚሁ አማልክት ናቸው፤ 9 ፍልስጥኤማውያን ሆይ፤ በርቱ ወንድነታችሁም ይታይ፤ አለዚያ ባሪያ እንዳደረጋችኋቸው ሁሉ፣ ዕብራውያን እናንተን መልሰው ባሪያ ያደርጓችኋል። ወንድነታችሁ ይታይ፤ ተዋጉ!” 10 ስለዚህ ፍልስጥኤማውያን ተዋጉ፤ እስራኤላውያንም ስለ ተሸነፉ እያንዳንዱ ወደየድንኳኑ ሸሸ። ታላቅ ዕልቂት ሆነ፤ ከእስራኤልም ሠላሳ ሺሕ እግረኛ ወታደሮች ወደቁ። 11 የእግዚአብሔር ታቦት ተማረከ፤ ሁለቱም የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ተገደሉ። የዔሊ መሞት 12 በዚያች ዕለት አንድ ብንያማዊ ልብሱን ቀዶ፣ በራሱም ላይ ትቢያ ነስንሶ፣ ከጦሩ ሜዳ እየበረረ ወደ ሴሎ መጣ። 13 እዚያ እንደ ደረሰም፣ ዔሊ ስለ እግዚአብሔር ታቦት ልቡ ስለ ተጨነቀ፣ በመንገድ ዳር ወንበሩ ላይ ተቀምጦ ይጠባበቅ ነበር። ሰውየውም ወደ ከተማው ገብቶ የሆነውን ሁሉ ባወራ ጊዜ፣ ከተማው ሁሉ በጩኸት ተናወጠ። 14 ዔሊም ጩኸቱን በሰማ ጊዜ፣ “የምን ጩኸት ነው?” ሲል ጠየቀ። ሰውየውም ፈጥኖ መጣና ለዔሊ ነገረው፤ 15 ዔሊ የዘጠና ስምንት ዓመት ሽማግሌ ስለ ነበር ዐይኖቹ ደክመው ማየት ተስኗቸው ነበር። 16 ሰውየውም ዔሊን፣ “ከጦሩ ሜዳ ገና አሁን መምጣቴ ነው፤ ከጦርነቱ አምልጬ የወጣሁትም ዛሬውኑ ነው” ብሎ ነገረው። ዔሊም፣ “ልጄ ሆይ፤ ታዲያ እንዴት ሆነ?” ሲል ጠየቀ። 17 ወሬውን ያመጣውም ሰው፣ “እስራኤል ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፤ ሰራዊቱም ከፍተኛ ዕልቂት ደርሶበታል፤ እንዲሁም ሁለቱ ልጆችህ አፍኒንና ፊንሐስ ሞተዋል፤ የእግዚአብሔርም የኪዳኑ ታቦት ተማርኳል” ብሎ መለሰለት። 18 ሰውየው ስለ እግዚአብሔር ታቦት በተናገረ ጊዜ፣ ዔሊ በቅጥሩ በር አጠገብ ከተቀመጠበት ወንበር ላይ በጀርባው ወደቀ፤ እርሱም ያረጀና ሰውነቱም የሚከብድ ስለ ነበር፣ ዐንገቱ ተሰብሮ ሞተ። እርሱም ለአርባ ዓመት በእስራኤል ላይ ፈራጅ ነበር። 19 በዚያ ጊዜ ምራቱ የፊንሐስ ሚስት፣ ነፍሰ ጡር ነበረች፤ የምትወልድበትም ጊዜ ተቃርቦ ነበር፣ የእግዚአብሔርን ታቦት መማረክ፣ የዐማቷንና የባሏንም መሞት በሰማች ጊዜ ምጡ ስለ ጠናባት ተንበርክካ ወለደች። 20 ለመሞትም በምታጣጥርበት ጊዜ፣ በአጠገቧ የነበሩት ሴቶች፣ “አይዞሽ፤ ወንድ ልጅ ወልደሻልና በርቺ” አሏት። እርሷ ግን መልስ አልሰጠችም፤ ልብ ብላም አላዳመጠችም። 21 የእግዚአብሔር ታቦት ስለ ተማረከ፣ ዐማቷና ባሏም ስለ ሞቱ፣ “ክብር ከእስራኤል ተለይቷል” ስትል የሕፃኑን ስም ኢካቦድ አለችው። 22 ከዚያም፣ “የእግዚአብሔር ታቦት ተማርኳልና ክብር ከእስራኤል ተለይቷል” አለች። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.