1 ሳሙኤል 31 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምየሳኦል መሞት 31፥1-13 ተጓ ምብ – 2ሳሙ 1፥4-12 ፤ 1ዜና 10፥1-12 1 በዚህ ጊዜ ፍልስጥኤማውያን እስራኤልን ወጉ፤ እስራኤላውያንም ከፊታቸው ሸሹ፤ ብዙዎቹም በጊልቦዓ ተራራ ላይ ተወግተው ወደቁ። 2 ፍልስጥኤማውያን ሳኦልንና ልጆቹን አጥብቀው አሳደዷቸው፤ የሳኦልንም ልጆች ዮናታንን፣ አሚናዳብንና ሜልኪሳን ገደሉ። 3 ውጊያው በሳኦል ላይ በረታበት፤ ቀስተኞችም ደርሰው ክፉኛ አቈሰሉት። 4 ሳኦልም ጋሻ ጃግሬውን፣ “እነዚህ ሸለፈታሞች መጥተው መሣለቂያ እንዳያደርጉኝ፣ ሰይፍህን መዝዘህ ውጋኝ” አለው። ጋሻ ጃግሬው ግን እጅግ ፈርቶ ስለ ነበር፣ ፈቃደኛ አልሆነም። ስለዚህ ሳኦል በገዛ ሰይፉ ላይ ወድቆ ሞተ። 5 ጋሻ ጃግሬውም ሳኦል መሞቱን ሲያይ፣ እርሱም በራሱ ሰይፍ ላይ ወድቆ ዐብሮት ሞተ። 6 ሳኦልና ሦስት ልጆቹ፣ ዐብረውት የነበሩ ሰዎች ሁሉና ጋሻ ጃግሬው የሞቱት በአንድ ላይ በዚያ ቀን ነበር። 7 በሸለቆው ማዶና ከዮርዳኖስ ባሻገር ያሉ እስራኤላውያን፣ የእስራኤል ሰራዊት መሸሹን፣ ሳኦልና ልጆቹም መሞታቸውን ሲያዩ፣ ከተሞቻቸውን ለቅቀው ሸሹ፤ ፍልስጥኤማውያንም መጥተው ተቀመጡባቸው። 8 በማግስቱ ፍልስጥኤማውያን የሞቱትን ለመግፈፍ ሲመጡ፣ ሳኦልና ሦስቱ ልጆቹ በጊልቦዓ ተራራ ላይ ወድቀው አገኟቸው። 9 ከዚያም የሳኦልን ራስ ቈርጠው፣ የጦር መሣሪያውንም ገፍፈው፣ ለቤተ ጣዖቶቻቸውና ለሕዝቡ የምሥራቹን እንዲናገሩ ወደ መላው የፍልስጥኤም ምድር መልክተኞችን ላኩ። 10 የጦር መሣሪያውን በአስታሮት ቤተ ጣዖት ውስጥ አስቀመጡት፤ ሬሳውን ደግሞ በቤትሳን ግንብ ላይ አንጠለጠሉት። 11 የኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች ፍልስጥኤማውያን በሳኦል ላይ ያደረጉትን በሰሙ ጊዜ፣ 12 ጀግኖቻቸው ሁሉ ተነሥተው ሌሊቱን ሙሉ ተጓዙ፤ የሳኦልንና የልጆቹን ሬሳ ከቤትሳን ግንብ ላይ አውርደው ወደ ኢያቢስ አምጥተው አቃጠሉ። 13 ከዚያም ዐጥንቶቻቸውን ወስደው በኢያቢስ ባለው የአጣጥ ዛፍ ሥር ቀበሩ፤ ሰባት ቀንም ጾሙ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.