Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


1 ሳሙኤል 29 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


አንኩስ ዳዊትን ወደ ጺቅላግ መልሶ መላኩ

1 ፍልስጥኤማውያን ሰራዊታቸውን ሁሉ በአፌቅ ሰበሰቡ፤ እስራኤላውያንም በኢይዝራኤል ሸለቆ ባለው ምንጭ አጠገብ ሰፈሩ፤

2 የፍልስጥኤማውያን ገዦች በመቶና በሺሕ ሆነው ሲዘምቱ፣ ዳዊትና ሰዎቹም ከአንኩስ ጋራ ደጀን ሆነው ይከተሉ ነበር።

3 የፍልስጥኤም አዛዦችም፣ “እነዚህ ዕብራውያን እዚህ ምን እያደረጉ ነው?” ብለው ጠየቁ። አንኩስም፣ “ይህ የእስራኤል ንጉሥ የሳኦል አገልጋይ የነበረው ዳዊት አይደለምን? ከእኔ ጋራ መኖር ከጀመረ እነሆ ዓመት ዐለፈው፤ እኔን ከተጠጋበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ምንም በደል አላገኘሁበትም” አላቸው።

4 የፍልስጥኤማውያን አዛዦች ግን በአንኩስ ላይ ተቈጥተው እንዲህ አሉ፤ “ይህን ሰው ወደዚያው ወደ ሰጠኸው ቦታ ይመለስ ዘንድ ስደደው፤ በውጊያው ጊዜ በእኛ ላይ ተመልሶ ጠላት እንዳይሆን፣ ዐብሮን ወደ ጦርነቱ መሄድ የለበትም፤ የእኛን ሰዎች ራስ ቈርጦ ካልወሰደ ከጌታው ጋራ እንዴት ሊታረቅ ይችላል?

5 በዘፈን እየተቀባበሉ፣ “ ‘ሳኦል ሺሕ ገደለ፤ ዳዊት ግን ዐሥር ሺሕ’ ብለው የዘመሩለት ይኸው ዳዊት አይደለምን?”

6 ስለዚህ አንኩስ ዳዊትን ጠርቶ እንዲህ አለው፤ “ሕያው እግዚአብሔርን አንተ ታማኝ ነህ፤ ወደ እኔ እዚህ ከመጣህበት ቀን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ምንም ጥፋት ያላገኘሁብህ ስለ ሆነ፣ ዐብረኸኝ ብትዘምት በበኩሌ ደስተኛ ነበርሁ፤ ነገር ግን ገዦቹ አልተቀበሉህም፤

7 እንግዲህ ተመልሰህ በሰላም ሂድ፤ የፍልስጥኤማውያንን ገዦች ደስ የማያሰኝ ምንም ነገር አታድርግ።”

8 ዳዊትም አንኩስን፣ “ለመሆኑ ምን አደረግሁ? እዚህ ከመጣሁበት ዕለት ጀምሮ እስካሁን ድረስ፣ በአገልጋይህ ላይ ምን አገኘህበት? ታዲያ፣ ከንጉሡ ከጌታዬ ጠላቶች ጋራ የማልዋጋው ስለ ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቀው።

9 አንኩስም እንዲህ አለው፤ “በእኔ ዘንድ እንደ እግዚአብሔር መልአክ መልካም እንደ ሆንህ ዐውቃለሁ፤ የፍልስጥኤማውያን አዛዦች ግን፣ ‘ዐብሮን ለጦርነት መውጣት የለበትም’ ብለዋል።

10 አሁንም ዐብረውህ ከመጡት ከጌታህ አገልጋዮች ጋራ ማለዳ ተነሡ፤ በጧት ፀሓይ እንደ ወጣችም ሂዱ” አለው።

11 ስለዚህ ዳዊትና ሰዎቹ ወደ ፍልስጥኤማውያን ምድር ለመመለስ በማለዳ ተነሡ፤ ፍልስጥኤማውያንም ወደ ኢይዝራኤል ወጡ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos