Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


1 ሳሙኤል 21 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ዳዊት ወደ ኖብ ሄደ

1 ዳዊትም ካህኑ አቢሜሌክ ወዳለበት ወደ ኖብ ሄደ። አቢሜሌክም እየተንቀጠቀጠ ዳዊትን ሊገናኘው መጣና፣ “ምነው ብቻህን? ሰውስ ለምን ዐብሮህ የለም?” ሲል ጠየቀው።

2 ዳዊት፣ ካህኑን አቢሜሌክን እንዲህ አለው፤ “ንጉሡ፣ ‘ስለ ላክሁህ ነገርና ስለ ሰጠሁህ መመሪያ ማንም ሰው ምንም ነገር አይወቅ’ ብሎ አዞኛል። ሰዎቼንም የት እንደምንገናኝ ነግሬያቸዋለሁ።

3 ታዲያ አሁን በእጅህ ምን አለ? ዐምስት እንጀራ ወይም የተገኘውን ማንኛውንም ነገር ስጠኝ።”

4 ካህኑም ዳዊትን፣ “ሰው ሁሉ የሚበላው እንጀራ የለኝም፤ ነገር ግን ሰዎቹ በቅርቡ ከሴት የተጠበቁ ከሆነ፣ የተቀደሰ እንጀራ በዚህ አለ” አለው።

5 ዳዊትም “እንደተለመደው ሁሉ ከወጣሁ ጊዜ ጀምሮ ሴቶች ከእኛ ተጠብቀዋል፤ ባልተቀደሰ ተልእኮ ውስጥ እንኳ የሰዎቹ ዕቃዎች የተቀደሱ ናቸው፤ ታዲያ ዛሬማ እንዴት!” ሲል ለካህኑ መለሰ።

6 ስለዚህ ካህኑ የተቀደሰውን እንጀራ ለዳዊት ሰጠው፤ ከእግዚአብሔር ፊት ተነሥቶ በትኵስ እንጀራ ከተተካው ከገጸ ኅብስቱ በቀር በዚያ ሌላ እንጀራ አልነበረምና።

7 በዚያችም ዕለት ከሳኦል አገልጋዮች አንዱና የእረኞቹ አለቃ የሆነው ኤዶማዊው ዶይቅ እዚያው በእግዚአብሔር ፊት እንዲቈይ ተገዶ ነበር።

8 ዳዊት አቢሜሌክን፣ “የንጉሡ ጕዳይ ስላስቸኰለኝ፣ ሰይፌንም ሆነ ሌላ የጦር መሣሪያ አላመጣሁም፤ እዚህ ካንተ ዘንድ ጦር ወይም ሰይፍ አይገኝምን?” ሲል ጠየቀው።

9 ካህኑም፣ “በኤላ ሸለቆ አንተ የገደልኸው የፍልስጥኤማዊው የጎልያድ ሰይፍ እዚህ አለ፤ ከኤፉዱ በስተኋላ በጨርቅ ተጠቅልሏል ከፈለግህ ውሰደው፤ ከርሱ በቀር ሌላ ሰይፍ እዚህ የለም” ብሎ መለሰለት። ዳዊትም “እንደ እርሱ ያለ የለምና እርሱኑ ስጠኝ” አለው።


ዳዊት ወደ ጌት ሄደ

10 በዚያች ዕለት ዳዊት ከሳኦል ሸሽቶ ወደ ጋት ንጉሥ ወደ አንኩስ ሄደ።

11 የአንኩስ አገልጋዮችም፣ “የምድሪቱ ንጉሥ ዳዊት ይህ አይደለምን? ደግሞስ፣ “ ‘ሳኦል ሺሕ ገደለ፤ ዳዊት ግን ዐሥር ሺሕ ገደለ’ ብለው በጭፈራቸው የዘፈኑለትስ እርሱ አይደለምን?” አሉት።

12 ዳዊት ነገሩን በልቡ አኖረ፤ የጋትን ንጉሥ አንኩስንም እጅግ ፈራው።

13 ስለዚህ በፊታቸው አእምሮውን እንደ ሳተ ሰው ሆነ፤ በያዙትም ጊዜ የከተማዪቱን ቅጥሮች እየቦጫጨረ፣ ልጋጉንም በጢሙ ላይ እያዝረበረበ እንደ እብድ ሆነ።

14 አንኩስም አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፤ “ሰውየውን እስኪ ተመልከቱት፤ እብድ እኮ ነው! ታዲያ ወደ እኔ ያመጣችሁት ለምንድን ነው?

15 በፊቴ እንዲህ ይሆን ዘንድ ይህን ሰው እዚህ ያመጣችሁት እብድ ዐጥቼ ነውን? እንዲህ ያለውስ ሰው ወደ ቤቴ መግባት ይገባዋልን?”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos