ሶፎንያስ 2 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየንስሓ ጥሪ 1 እናንተ የማታፍሩ ሕዝቦች በፍጥነት ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ፤ 2 አለበለዚያ ግን ነፋስ ጠራርጎ እንደሚወስደው ገለባ ትሆናላችሁ፤ እንደ እሳት የሚነደው የእግዚአብሔር ቊጣ ይመጣባችኋል፤ ኀይለኛው የእግዚአብሔር የቊጣ ቀን ይመጣባችኋል። 3 ትእዛዞቹን የምትፈጽሙ፥ በምድሪቱ የምትኖሩ፥ እናንተ ትሑታን ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ፤ የጽድቅን ሥራ ሥሩ፤ በትሕትናም ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ በዚህም ሁኔታ እግዚአብሔር ቊጣውን በሚገልጥበት ቀን ምናልባት ከቅጣት ታመልጡ ይሆናል። በሌሎች ሕዝቦች ላይ የተላለፈ ፍርድ 4 ጋዛ ተለቃ ሰው የማይኖርባት ትሆናለች፤ አስቀሎናም ባድማ ትሆናለች፤ የአሽዶድ ነዋሪዎች በቀትር ከመኖሪያቸው ይባረራሉ፤ የዓቃሮንም ሰዎች ከከተማይቱ ተፈናቅለው ይወጣሉ። 5 እናንተ በባሕር ዳር የምትኖሩ ከሪታውያን ማለት ፍልስጥኤማውያን ወዮላችሁ! የእግዚአብሔር ፍርድ በእናንተ ላይ ደርሷል፤ የፍልስጥኤም ምድር ለሆንሽው ከነዓን ወዮልሽ አንድ እንኳ ነዋሪ እንዳይኖርብሽ አድርጌ አጠፋሻለሁ። 6 በባሕር ዳር ያለው ምድራችሁ የከብት ማሰማሪያ፥ የእረኞች መኖሪያና የመንጋዎች ማደሪያ በረት ይሆናል። 7 እግዚአብሔር አምላካቸው ስለሚንከባከባቸውና ንብረታቸውን ስለሚመልስላቸው ከብቶቻቸውን ያሰማሩበት ዘንድ የባሕሩ ዳር ከይሁዳ ሕዝብ ለተረፉት ርስት ይሆናል፤ በየምሽቱም በአስቀሎና ቤቶች ያድራሉ። 8 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በሕዝቤ ላይ የደረሰውን የሞአብን ሕዝብ ፌዝና የአሞንን ሕዝብ ስድብ ሰምቼአለሁ፤ እነርሱም እንዴት አድርገው እንዳፌዙባቸውና ርስታቸውንም ለመውሰድ እንደ ዛቱባቸው ዐውቄአለሁ። 9 እኔ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሕያው እንደ መሆኔ፥ ሞአብ እንደ ሰዶም አሞንም እንደ ገሞራ ይሆናሉ፤ ምድሪቱም በዳዋና በጨው ጒድጓድ ተወራ ለዘለቄታ ባድማ ትሆናለች፤ ከሞት የተረፈው ሕዝቤ ይበዘብዛቸዋል ንብረታቸውንም ይወርሳል።” 10 የሞአብና የዐሞን ሕዝብ በሠራዊት አምላክ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ስላፌዙና ስለ ዛቱ ይህ ቅጣት የሚደርስባቸው ለትዕቢታቸው አጸፋ የሚከፈል ዕድል ፈንታቸው ስለ ሆነ ነው። 11 በምድራቸው ያሉትን ሐሰተኞች አማልክት ሁሉ በማጥፋቱ እግዚአብሔር በእነርሱ ዘንድ የተፈራ ይሆናል፤ በባሕር ጠረፍና በደሴቶች የሚኖሩ መንግሥታት ሁሉ በያሉበት ለእርሱ ይሰግዳሉ። 12 እናንተም ኢትዮጵያውያን በሰይፌ ትገደላላችሁ። 13 እግዚአብሔር በኀይሉ በሰሜን የምትገኘውን አሦርን ያጠፋል፤ የነነዌን ከተማ ባድማ ያደርጋታል፤ እንደ ምድረ በዳም ያደርቃታል። 14 የአራዊት መንጋዎች በእርስዋ ይኖራሉ፤ ልዩ ልዩ ዐይነት ጒጒቶች በጒልላትዋ ላይ ይኖራሉ፤ በየመስኮቱም ይጮኻሉ፤ በሊባኖስ ዛፍ የተሠራው ወለል ስለሚላቀቅ በመድረኩ ላይ ጥፋት ይደርሳል። 15 “ከእኔ በቀር ሌላ የለም” ብላ በመዝናናትና ራስዋን በማስደሰት ትኖር የነበረችው ከተማ እንዴት የአራዊት መመሰጊያ ባድማ ሆነች! በእርስዋ በኩል የሚያልፈው ሁሉ በእጁ እየጠቈመ ያፏጭባታል። |