Biblia Todo Logo
La Biblia Online

- Anuncios -


ዘካርያስ 3 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ነቢዩ ዘካርያስ ስለ ሊቀ ካህናቱ ያየው ራእይ

1 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ሊቀ ካህናቱን ኢያሱን በእግዚአብሔር መልአክ ፊት ቆሞ በራእይ አሳየኝ፤ ሰይጣንም ኢያሱን ለመክሰስ በስተቀኙ ቆሞ ነበር።

2 የእግዚአብሔርም መልአክ ሰይጣንን “አንተ ሰይጣን! እግዚአብሔር ይገሥጽህ! ኢየሩሳሌምን የሚወድ እግዚአብሔር ይገሥጽህ! ይህ ሰው እኮ ከእሳት ውስጥ ተርፎ እንደ ወጣ እንጨት ነው” አለው።

3 ኢያሱም ያደፈ ልብስ ለብሶ በመልአኩ ፊት ቆሞ ነበር።

4 መልአኩም በፊቱ ቆመው የሚያገለግሉትን “ይህን ያደፈ ልብስ አውልቁለት!” ብሎ አዘዛቸው፤ ወደ ኢያሱም መለስ ብሎ “እነሆ በደልህን አስወግጄልሃለሁ፤ አዲስ የክብር ልብስም አለብስሃለሁ” አለው።

5 መልአኩም አገልጋዮቹን “ንጹሕ ጥምጥም በራሱ ላይ አድርጉለት!” ብሎ አዘዘ፤ እነርሱም እንደ ታዘዙት አደረጉ፤ የእግዚአብሔር መልአክ እዚያው ቆሞ እንዳለ አገልጋዮቹ ኢያሱን አዲስ ልብስ አለበሱት።

6 ከዚህ በኋላ መልአኩ ኢያሱን በማስጠንቀቅ፦

7 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል አለው፦ “አካሄድህ እንደኔ ፈቃድ ቢሆን፥ ያዘዝኩህንም ሁሉ ብታደርግ፥ በቤተ መቅደሴ የአስተዳዳሪነትን፥ በአደባባዮቼም የበላይነትን ሥልጣን እሰጥሃለሁ፤ እዚህ ከቆሙት መላእክት ጋር በእኔ ፊት መግባትና መውጣት እንድትችል ባለሟልነትን እሰጥሃለሁ።

8 ሊቀ ካህናት ኢያሱ ሆይ! ይህን ስማ፤ እናንተም ከእርሱ ጋር በክህነት የምታገለግሉና ወደ ፊት ለሚሆነው መልካም ነገር ምልክት የምትሆኑ ይህን አድምጡ፤ ‘ቅርንጫፍ’ ተብሎ የሚጠራውን አገልጋዬን ወደ ፊት እልካለሁ።

9 እነሆ፥ በኢያሱ ፊት ሰባት ቅርጽ ያለው አንድ ድንጋይ አኖራለሁ፤ በእርሱም ላይ የጽሑፍ መግለጫ እቀርጻለሁ፤ የዚህችንም አገር በደል በአንድ ቀን አስወግዳለሁ።

10 ያም ቀን ሲደርስ ከእናንተ እያንዳንዱ በወይኑና በበለሱ ተክል ሥር ጐረቤቱን ግብዣ እየጠራ ተድላ ደስታ ያደርጋል።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos