ሩት 4 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየቦዔዝና የሩት ጋብቻ 1 ቦዔዝ በከተማው በር አጠገብ ወደሚገኘው መሰብሰቢያ አደባባይ ሄዶ ተቀመጠ፤ ከዚህ በፊት ቦዔዝ ስለ እርሱ የተናገረው የአቤሜሌክ የቅርብ ዘመድ ወደዚያው ቦታ መጣ፤ ቦዔዝም በስሙ ጠርቶ “ወንድሜ ሆይ! ወደዚህ መጥተህ አጠገቤ ተቀመጥ” አለው። እርሱም ወደዚያ ሄዶ ተቀመጠ። 2 ከዚህ በኋላ ቦዔዝ ከከተማው ሽማግሌዎች ዐሥሩን መርጦ “እዚህ ተቀመጡ” አላቸው፤ እነርሱም ተቀመጡ። 3 ቦዔዝም የቅርብ ዘመድ የሆነውን ሰው እንዲህ አለው፦ “እነሆ ናዖሚ ከሞአብ አገር ተመልሳ መጥታለች፤ የዘመዳችንን የአቤሜሌክንም መሬት መሸጥ ትፈልጋለች፤ 4 አንተም ስለዚህ ጉዳይ ማወቅ የሚገባህ ይመስለኛል፤ እንግዲህ መሬቱን ከፈለግኸው እዚህ በተቀመጡትና በሕዝቤ ሽማግሌዎች ፊት ለራስህ ልታስቀረው ትችላለህ፤ የማትፈልገው ከሆነ ግን ቊርጡን ንገረኝ፤ መሬቱን የማስቀረት ቅድሚያ ያለህ አንተ ነህ፤ ከአንተም ቀጥሎ እኔ ነኝ።” ሰውየውም “እኔ አስቀረዋለሁ” አለ። 5 ቦዔዝም “መሬቱን ከናዖሚ የምትገዛ ከሆነ በውርሱ የሟቹን ስም ታስጠራ ዘንድ ባልዋ የሞተባትን ሞአባዊትዋን ሩትንም አብረህ ትወስዳለህ” አለው። 6 ሰውየውም “ይህን ብወስድ የራሴን ድርሻ የሚጐዳ ስለ ሆነ እኔ ልወስደው አልፈልግምና አንተ እንድትወስደው ፈቅጄልሃለሁ” አለው። 7 በቀድሞ ዘመን በእስራኤላውያን ዘንድ የመግዛትና የመሽጥ፥ እንዲሁም ንብረትን የማስተላለፍ ልማድ እንዲህ ነበር፤ ውሉን ለማጽደቅ አንዱ ወገን ጫማውን አውልቆ ለሌላው ወገን ይሰጥ ነበር፤ ይህም በእስራኤላውያን ዘንድ ውል ለመፈጸሙ ማረጋገጫ ነበር። 8 ስለዚህ ሰውየው ቦዔዝን “አንተ ልታስቀረው ትችላለህ” ብሎ ጫማውን አውልቆ ሰጠው። 9 ከዚህ በኋላ ቦዔዝ ለሽማግሌዎቹና እዚያ ለነበሩት ሁሉ እንዲህ አለ፦ “እነሆ! የአቤሜሌክንና የልጆቹን የኬሊዎንና የማሕሎንን ንብረት ሁሉ ዛሬ ከናዖሚ በውርስ እንዳስቀረሁት እናንተ ሁላችሁ ምስክሮች ናችሁ፤ 10 በተጨማሪም የሟቹ የማሕሎን ሚስት ሞአባዊቷ ሩት ሚስቴ ትሆናለች፤ ይህም ንብረቱ ከሟቹ ቤተሰብ እንዳይወጣና የትውልድ ሐረጉም ከወንድሞቹ መካከልና ከሀገሩ አደባባይ እንዳይጠፉ ያደርገዋል፤ ለዚህ ሁሉ ዛሬ እናንተ ምስክሮች ናችሁ።” 11 በአደባባይ ተቀምጠው የነበሩት ሽማግሌዎችና ሌሎችም ሰዎች እንዲህ አሉ፥ “አዎ፥ እኛ ለዚህ ነገር ምስክሮች ነን፤ እግዚአብሔር ይህችን ሚስትህን ብዙ ልጆችን በመውለድ የያዕቆብን ቤት እንደ መሠረቱት እንደ ራሔልና እንደ ልያ ያድርግልህ፤ እግዚአብሔር በኤፍራታ ያበልጽግህ፤ በቤተልሔምም ዝነኛ ያድርግህ፤ 12 እግዚአብሔር ከዚህች ወጣት ሴት የሚሰጥህን ልጆች ይባርክልህ፤ ቤተሰብህንም ከይሁዳና ከትዕማር እንደተወለደው እንደ ፋሬስ ቤተሰብ ያድርግልህ።” የዳዊት የትውልድ ሐረግ 13 በዚህ ሁኔታ ቦዔዝ ሩትን ሚስት አድርጎ ወደ ቤቱ ወሰዳት፤ በተገናኙም ጊዜ እግዚአብሔር ፀንሳ ወንድ ልጅ እንድትወልድ አደረጋት። 14 ሴቶች ናዖሚን እንዲህ አሉአት፦ “ዛሬ ወራሽና ጧሪ ያላሳጣሽ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን! እግዚአብሔር ይህን ልጅ በእስራኤል ዝነኛ ያድርገው! 15 ምራትሽ በጣም ትወድሻለች፤ ሰባት ልጆች ከሚያደርጉልሽ የበለጠ አድርጋልሻለች፤ አሁን ደግሞ ሕይወትሽን የሚያድስልሽና በእርጅናሽ ወራት የሚጦርሽን ወንድ ልጅ ወልዳልሻለች።” 16 ናዖሚም ይህን ሕፃን አቀፈችው፤ ተንከባክባም አሳደገችው። 17 የጐረቤት ሴቶች ልጁን “ኢዮቤድ” ብለው ስም አወጡለት፤ “ለናዖሚ ወንድ ልጅ ተወለደላት!” እያሉም ለሰው ሁሉ አወሩ። የንጉሥ ዳዊት አባት የሆነውን እሴይን የወለደ ይኸው ኢዮቤድ ነው። 18-22 ከፋሬስ አንሥቶ እስከ ዳዊት ያለው የትውልድ ሐረግ የሚከተለው ነው፤ ፋሬስ ሔጽሮንን ወለደ፤ ሔጽሮን አራምን ወለደ፤ አራም ዐሚናዳብን ወለደ፤ ዐሚናዳብ ነአሶንን ወለደ፤ ነአሶን ሰልሞንን ወለደ፤ ሰልሞን ቦዔዝን ወለደ፤ ቦዔዝ ኢዮቤድን ወለደ፤ ኢዮቤድ እሴይን ወለደ፤ እሴይም ዳዊትን ወለደ። |