Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ሩት 3 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ሩት ባል ማግኘትዋ

1 አማትዋ ናዖሚ ሩትን እንዲህ አለቻት፦ “ልጄ ሆይ! መልካም ይሆንልሽ ዘንድ የተመቻቸ ኑሮ የምትኖሪበትን ሁናቴ ልፈልግልሽ ይገባል።

2 ስትቃርሚ አብረውሽ የነበሩት ሴቶች የሚያገለግሉት ቦዔዝ የቅርብ ዘመዳችን ነው፤ እነሆ! እርሱ ዛሬ ማታ ገብስ ይወቃል፤

3 ስለዚህ ሰውነትሽን ታጠቢና ሽቶ ተቀቢ፤ የክት ልብስሽንም ልበሺ፤ ከዚህ በኋላ እርሱ ገብሱን ወደሚወቃበት አውድማ ሂጂ፤ ነገር ግን እስከሚበላና እስከሚጠጣ ድረስ በፊቱ አትታዪ።

4 የት እንደሚተኛ ካረጋገጥሽ በኋላ፥ እንቅልፍ ሲወስደው ወደ እርሱ ቀረብ በዪና ከግርጌው በኩል ልብሱን ገልጠሽ በእግሩ አጠገብ ተኚ፤ ምን ማድረግ እንደሚገባሽ እርሱ ራሱ ይነግርሻል።”

5 ሩትም “ያልሽውን ሁሉ አደርጋለሁ” አለቻት።

6 ስለዚህ ሩት ወደ አውድማው ሄዳ ልክ ዐማትዋ እንደ ነገረቻት አደረገች።

7 ቦዔዝ ከበላና ከጠጣ በኋላ ደስ ብሎት ነበር፤ ወደ ገብሱም ክምር ሄዶ ጋደም አለና አንቀላፋ፤ ሩትም በቀስታ ወደ እርሱ ተጠጋች፤ ልብሱንም ገለጥ አድርጋ በእግሩ አጠገብ ተኛች።

8 ወደ እኩለ ሌሊት ገደማም ቦዔዝ ድንገት ነቅቶ ሲገላበጥ አንዲት ሴት በግርጌ ተኝታ በማግኘቱ ተደነቀ፤

9 “አንቺ ማን ነሽ?” ብሎም ጠየቃት። እርስዋም “ጌታዬ ሆይ! አገልጋይህ እኔ ሩት ነኝ፤ አንተ የቅርብ ዘመድ ስለ ሆንክ ለእኔ ኑሮ የማሰብ ኀላፊነት አለብህ፤ ስለዚህ ልብስህን ባገልጋይህ ላይ ጣል አለችው።”

10 ቦዔዝም እንዲህ አላት፤ “ልጄ ሆይ! እግዚአብሔር ይባርክሽ፤ አሁን በምታደርጊው ነገር ከዚህ በፊት ለዐማትሽ ካደረግሽው የሚበልጥ ታማኝነት አሳይተሻል፤ ብትፈልጊ ኖሮ ወደ ሀብታም ወይም ወደ ድኻ ወጣት መሄድ ትችይ ነበር፤ ነገር ግን ይህን ማድረግ አልፈለግሽም፤

11 ልጄ ሆይ! አትፍሪ፤ ከእንግዲህ ወዲህ በከተማው ያሉ ሰዎች ሁሉ አንቺ መልካም ሴት መሆንሽን ያውቃሉ፤ የምትፈልጊውን ሁሉ አደርግልሻለሁ።

12 እኔ የቅርብ ዘመድ መሆኔ እውነት ነው፤ ነገር ግን ከእኔ ይልቅ ቅርብ የሆነ ሌላ ዘመድ አለ፤

13 እስኪነጋ እዚሁ ቈዪ! ሲነጋም ያ ሰው ስለ አንቺ ኀላፊነትን የሚወስድ መሆኑን ወይም አለመሆኑን እጠይቀዋለሁ፤ እርሱ ኀላፊነትን የሚወስድ ከሆነ መልካም ነው፤ የማይወስድ ከሆነ ግን ስለ አንቺ ኀላፊነትን እኔ እንደምወስድ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ፤ አሁንም ተኚ፤ እስኪነጋም ድረስ እዚሁ ቈዪ።”

14 ስለዚህ ሩት በቦዔዝ እግር አጠገብ ተኛች፤ ነገር ግን ቦዔዝ ወደ ዐውድማው እንደ መጣች ማንም እንዲያውቅ ስላልፈለገ ማንም ሊያያት በማይችልበት ሰዓት በማለዳ ከመኝታዋ ተነሣች።

15 ቦዔዝም “ሸማሽን ከላይሽ አንሺና ወደዚህ ዘርጊው” አላት። እርስዋም ሸማዋን ዘረጋች፤ ቦዔዝም ወደ ኻያ ኪሎ የሚጠጋ ገብስ ሰፈረላትና አንሥቶ በትከሻዋ አሸከማት። ከዚያም እርሱ ወደ ከተማ ሄደ።

16 ወደ ዐማትዋም በመጣች ጊዜ ዐማትዋ “ልጄ ሆይ! ያ ጉዳይ እንዴት ሆነልሽ?” አለቻት። ሩትም ቦዔዝ ያደረገላትን ሁሉ ነገረቻት።

17 ደግሞም “ወደ ዐማትሽ ባዶ እጅሽን አትሂጂ” ብሎ ይህን ኻያ ኪሎ ገብስ ሰጠኝ አለቻት።

18 ናዖሚም “ልጄ ሆይ! ሰውዬው ይህን ነገር ዛሬ እስኪፈጽም ድረስ አያርፍምና፥ ፍጻሜው እስኪታወቅ ድረስ ጠብቂ” አለቻት።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos