Biblia Todo Logo
La Biblia Online

- Anuncios -


ራእይ 4 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የእግዚአብሔር ዙፋንና ሰማያዊው የጸሎት ሥነ ሥርዓት

1 ከዚህ በኋላ ተመለከትኩ፤ እነሆ በሰማይ የተከፈተ በር ነበር፤ በመጀመሪያ ሰምቼው የነበረው እንደ እምቢልታ ያለው ድምፅ እንዲህ አለ፦ “ና ወደዚህ ውጣ፤ ወደፊት መሆን የሚገባቸውን ነገሮች አሳይሃለሁ፤”

2 ወዲያውኑ በመንፈስ ተመሰጥሁ፤ እነሆ በሰማይ ዙፋን አየሁ፤ በዙፋኑም ላይ አንድ አካል ተቀምጦበት ነበር።

3 በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ የነበረው መልኩ የኢያሰጲድንና የሰርዲኖን ዕንቊ ይመስል ነበር፤ በዙፋኑም ዙሪያ የመረግድ ዕንቊ የመሰለ ቀስተ ደመና ነበረ፤

4 እንዲሁም፥ በዙፋኑ ዙሪያ ኻያ አራት ዙፋኖች ነበሩ፤ በዙፋኖቹም ላይ ነጭ ልብስ የለበሱና በራሳቸው ላይ የወርቅ አክሊል የደፉ ኻያ አራት ሽማግሌዎች ተቀምጠው ነበር።

5 ከዙፋኑም መብረቅና ድምፅ ነጐድጓድም ይወጡ ነበር፤ በዙፋኑ ፊት የሚበሩ ሰባት ችቦዎች ነበሩ፤ እነርሱ ሰባቱ የእግዚአብሔር መንፈሶች ናቸው።

6 በዙፋኑ ፊት ጥርት ያለ የሚያንጸባርቅ የመስተዋት ባሕር ነበረ፤ በመካከል፥ በዙፋኑ ዙሪያ በስተፊትና በስተኋላ ብዙ ዐይኖች ያሉአቸው አራት እንስሶች ነበሩ።

7 የመጀመሪያው እንስሳ አንበሳ ይመስል ነበር፤ ሁለተኛው በሬ ይመስል ነበር፤ ሦስተኛው የሰው ፊት የሚመስል ፊት ነበረው፤ አራተኛው የሚበር ንስር ይመስል ነበር።

8 አራቱም እንስሶች እያንዳንዳቸው ስድስት ክንፎች ነበሩአቸው፤ በዙሪያቸውና በውስጣቸውም ዐይኖች ሞልተውባቸዋል፤ ሌሊትና ቀን፦ “ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ ሁሉን የሚችል ጌታ አምላክ፥ የነበረ፥ ያለና የሚመጣውም” ከማለት አያቋርጡም ነበር።

9 እንስሶቹ በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠውና ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ለሚኖረው ገናናነት፥ ክብርና ምስጋና በሚያቀርቡበት ጊዜ ሁሉ፥

10 ኻያ አራቱ ሽማግሌዎች ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም በሚኖረው፥ በዙፋኑ ላይ በተቀመጠው ፊት በግንባራቸው ተደፍተው ይሰግዳሉ፤ አክሊሎቻቸውንም በዙፋኑ ፊት አኑረው፥ እንዲህ ይላሉ፦

11 “ጌታችንና አምላካችን ሆይ፥ ሁሉን ነገር ስለ ፈጠርክ ሁሉም ነገር የተፈጠረውና የሚኖረው (ሕይወትን ያገኘው) በአንተ ፈቃድ ስለ ሆነ ገናናነት፥ ክብርና ኀይልም ለአንተ ይገባል” ይሉ ነበር።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos