መዝሙር 98 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምእግዚአብሔር የዓለም ገዢ ነው 1 ድንቅ ነገሮችን ስላደረገና፥ በኀያል ሥልጣኑ ድልን ስለ ተጐናጸፈ፥ ለእግዚአብሔር አዲስ መዝሙር ዘምሩለት! 2 እግዚአብሔር አዳኝነቱ እንዲታወቅ አደረገ፤ ጽድቁንም ለአሕዛብ ገለጠ። 3 ለእስራኤል ሕዝብ የሰጠውን ፍቅርና ታማኝነት አስታውሶአል፤ በየስፍራው ያሉ ሕዝቦች ሁሉ የአምላካችንን ድል አድራጊነት አይተዋል። 4 በምድር ላይ የምትኖሩ ሕዝቦች ሁሉ ለእግዚአብሔር በደስታ ዘምሩ! በመዝሙርና በእልልታ አመስግኑት! 5 በገና በመደርደርና በመዘመር ለእግዚአብሔር ምስጋና አቅርቡ! 6 ለንጉሣችን ለእግዚአብሔር አስደሳች የጥሩንባና የቀንደ መለከት ድምፅ አሰሙ። 7 ባሕርና በውስጥዋ ያላችሁ ፍጥረቶች ሁሉ ድምፃችሁን አሰሙ፤ ዓለምና በእርስዋ የምትኖሩ ሁሉ ዘምሩ! 8 እናንተ ወንዞች አጨብጭቡ፤ እናንተ ተራራዎች በእግዚአብሔር ፊት እልል እያላችሁ በአንድነት ዘምሩ። 9 እግዚአብሔር በምድር ላይ ሊፈርድ ስለሚመጣ በፊቱ ይዘምሩ፤ እርሱም በዓለም ላይ በጽድቅ፥ በሕዝቦች ላይ በትክክል ይፈርዳል። |