መዝሙር 96 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምእግዚአብሔር ከሁሉ በላይ መሆኑ ( 1ዜ.መ. 16፥23-33 ) 1 ለእግዚአብሔር አዲስ መዝሙር ዘምሩ! በምድር የምትኖሩ ሕዝቦች ሁሉ ለእግዚአብሔር ዘምሩ! 2 ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ አመስግኑትም! የአዳኝነቱን መልካም ዜና በየቀኑ አብሥሩ! 3 በሕዝቦች መካከል ክብሩን አስታውቁ፤ ለሕዝቦችም ሁሉ ታላቅ ሥራውን አውሩ! 4 እግዚአብሔር ታላቅ ነው፤ ከፍ ያለ ምስጋናም ይገባዋል፤ ከአማልክትም ሁሉ ይበልጥ ሊፈራ ይገባዋል። 5 ሌሎች ሕዝቦች የሚሰግዱላቸው አማልክት ጣዖቶች ናቸው፤ እግዚአብሔር ግን ሰማያትን የፈጠረ አምላክ ነው። 6 በዙሪያው ያለው ክብርና ግርማ ነው፤ ኀይልና ውበትም በመቅደሱ ውስጥ ናቸው። 7 በምድር የምትኖሩ ሕዝቦች ሁሉ! ስለ ክብሩና ስለ ኀይሉ እግዚአብሔርን አመስግኑት። 8 ለስሙ ተገቢ የሆነውን ክብር ለእግዚአብሔር ስጡ፤ ወደ መቅደሱም አደባባይ መባ ይዛችሁ ቅረቡ። 9 ግርማ በተመላ ቅድስናው ለእግዚአብሔር ስገዱ! የምድር ሕዝቦች ሁሉ በፊቱ ተንቀጥቀጡ! 10 በሕዝቦች መካከል “እግዚአብሔር ንጉሥ ነው! ምድር በጽኑ ስለ ተመሠረተች አትናወጥም፤ እርሱ ለሕዝቦች ሁሉ በትክክል ይፈርዳል” በሉ። 11 ሰማይና ምድር ደስ ይበላቸው! ባሕርና በውስጡ ያሉት ሁሉ እልል ይበሉ! 12 ማሳና በላይዋ የሚገኙ ሰብሎች ሁሉ ደስ ይበላቸው! ከዚያም የደን ዛፎች ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት በደስታ ይዘምሩ፤ 13 እርሱም በምድር ላይ ሊፈርድ ይመጣል፤ በዓለም ላይ በጽድቅ፥ በሰዎች ላይ በእውነተኛነቱ ይፈርዳል። |