Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


መዝሙር 92 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የምስጋና መዝሙር

1 ልዑል እግዚአብሔር ሆይ! አንተን ማመስገንና የምስጋና መዝሙር ለአንተ ማቅረብ መልካም ነው።

2 ስለ ዘለዓለማዊው ፍቅርህ በየማለዳው መናገር፥ ስለ ታማኝነትህ በየሌሊቱ ማውራት፥ እንዴት መልካም ነው?

3 ባለ አውታር በሆኑት የሙዚቃ መሣሪያዎችና በበገና ቅኝት አንተን ማመስገን እንዴት መልካም ነው?

4 እግዚአብሔር ሆይ፥ የአንተ ታላላቅ ሥራዎች ደስ ያሰኙኛል፤ አንተ ስላደረግኻቸውም ነገሮች በደስታ እዘምራለሁ።

5 እግዚአብሔር ሆይ! ሥራህ እንዴት ታላቅ ነው! ሐሳብህስ እንዴት ጥልቅ ነው!

6 ይህ ነገር የማይገባው አላዋቂ ለሆነ ሰው ነው፤ ሞኝ ሰውም ቢሆን አይገባውም።

7 ክፉዎች እንደ ሣር ቶሎ ቢያድጉም፥ ክፉ አድራጊዎች ቢበለጽጉም፥ እነርሱ ለዘለዓለሙ ይጠፋሉ።

8 አንተ ግን እግዚአብሔር ሆይ! ለዘለዓለም የሁሉ በላይ ነህ።

9 እግዚአብሔር ሆይ! ጠላቶችህ ይጠፋሉ፤ ክፉ አድራጊዎችም ሁሉ ይበተናሉ።

10 አንተ እንደ ጐሽ ቀንድ ከፍ አደረግኸኝ፤ በትኲስ ዘይትም ቀባኸኝ።

11 የጠላቶቼን መሸነፍ አየሁ፤ የአስጨናቂዎቼንም ውድቀት ሰማሁ።

12 ደጋግ ሰዎች እንደ ዘንባባ ዛፍ ይለመልማሉ፤ እንደ ሊባኖስ ዛፍም ያድጋሉ።

13 በእግዚአብሔር ቤት ተተክለው በቤተ መቅደስ አደባባይ ውስጥ ተመችቶአቸው ይኖራሉ።

14 በእርጅና ዘመናቸው እንኳ ባለማቋረጥ እንደሚያፈሩ፥ ዘወትርም አረንጓዴ እንደ ሆኑ ዛፎች ይሆናሉ።

15 ይህም የሚያረጋግጠው እግዚአብሔር ትክክለኛ መሆኑንና ጠባቂዬ በሆነው አምላክ ዘንድ እንከን ያለመኖሩን ነው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos