መዝሙር 85 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምስለ ሕዝብ ሰላም የሚቀርብ ጸሎት 1 እግዚአብሔር ሆይ! ለምድርህ ምሕረትን አሳየህ፤ የያዕቆብን ዘር እንደገና አበለጸግህ። 2 የሕዝብህን በደል ይቅር አልክ፤ ኃጢአታቸውንም ሁሉ ደመሰስክ። 3 እነርሱን ከመቈጣት ታገሥህ፤ ብርቱ ቊጣህንም መለስህ። 4 አዳኛችን እግዚአብሔር ሆይ! ከተሰደድንበት መልሰን፤ በእኛም ላይ ያለህን ቅርታ አርቅልን። 5 በእኛ ላይ የምትቈጣው ለዘለዓለም ነውን? ቊጣህንስ ከትውልድ ወደ ትውልድ ታስተላልፋለህን? 6 እኛ ሕዝብህ በአንተ እንደሰት ዘንድ፥ እንደገና ሕይወትን አትዘራብንምን? 7 እግዚአብሔር ሆይ! ዘለዓለማዊ ፍቅርህን አሳየን፤ አድነንም። 8 እግዚአብሔር አምላክ የሚናገረውን ቃል ልስማ፤ እንደገና በስሕተት መንገድ ካልሄዱ በቀር፥ ለሕዝቡና ለታማኞቹ ሰላምን እንደሚሰጥ ተስፋ ሰጥቶአል። 9 ክብሩ በምድራችን ይኖር ዘንድ፥ እርሱን ለሚፈሩት አዳኝነቱ ቅርብ ነው። 10 ፍቅርና እውነት ይተቃቀፋሉ፤ ጽድቅና ሰላም ይስማማሉ። 11 የሰው ታማኝነት ከምድር ይፈልቃል ጽድቅም ከሰማይ ወደ ታች ይመለከታል። 12 እግዚአብሔር ያበለጽገናል፤ ምድራችንም ብዙ የመከር ፍሬ ትሰጠናለች። 13 ፈለጉን እንከተል ዘንድ ጽድቅ በእግዚአብሔር ፊት ይሄዳል። |