መዝሙር 8 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየእግዚአብሔር ታላቅነትና የሰው ክብር 1 ጌታችንና እግዚአብሔር ሆይ! ስምህ በዓለም ሁሉ የገነነ ነው። ክብርህንም ከሰማያት ሁሉ በላይ አድርገሃል። 2 በጠላቶችህ ምክንያት ጠላትንና ተበቃይን ዝም ለማሰኘት ከልጆችና ጡት ከሚጠቡ አፍ፥ ምስጋናን አዘጋጀህ። 3 አንተ የፈጠርከውን ሰማይ በማይበት ጊዜ፥ በየስፍራቸው አጽንተህ ያኖርካቸውን ጨረቃንና ኮከቦችን በምመለከትበት ጊዜ፥ 4 አንተ እርሱን ታስበው ዘንድ ሰው ምንድን ነው? እርሱንስ ትጐበኘው ዘንድ የሰው ልጅ ምንድን ነው? 5 ከመላእክት በጥቂቱ ብታሳንሰውም፥ የክብርና የምስጋና ዘውድ ጫንክለት፤ 6 በፈጠርካቸው ፍጥረቶች ሁሉ ላይ፥ ገዢ አድርገህ ሾምከው፤ ከፍጥረትም ሁሉ በላይ አደረግኸው። 7 በጎችንና ከብቶችን፥ የዱር አራዊትንም፥ 8 የሰማይ ወፎችንና የባሕር ዓሣዎችን፥ በባሕር ውስጥ ያሉ ፍጥረቶችን ሁሉ አስገዛህለት። 9 ጌታችን እግዚአብሔር ሆይ! ስምህ በዓለም ሁሉ የገነነ ነው! |