መዝሙር 65 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምክብርና ምስጋና ለእግዚአብሔር ማቅረብ 1 አምላክ ሆይ! በጽዮን ሆነን አንተን ማመስገን፤ ለአንተ የተሳልነውንም መስጠት ይገባናል። 2 አንተ ጸሎትን ሰሚ ስለ ሆንክ ሰዎች ሁሉ ወደ አንተ ይመጣሉ። 3 ኃጢአት በላያችን በርትቶብን ነበር፤ አንተ ግን በደላችንን ሁሉ ይቅር አልክልን። 4 አንተ የመረጥካቸውና በተቀደሰ አደባባይህ እንዲኖሩ ወደ ራስህ ያቀረብካቸው፥ ደስ ይበላቸው፤ እኛም ከቤትህ በሚገኘው መልካም ነገርና ከመቅደስህ በሚገኘው በረከት እንረካለን። 5 ጸሎታችንን ሰምተህ ድልን ታጐናጽፈናለህ፤ እኛንም ለማዳን ብዙ ድንቅ ነገሮችን ታደርጋለህ፤ ሩቅ ከሆነው ባሕር ማዶ ያሉት ሳይቀሩ የዓለም ሕዝቦች ሁሉ በአንተ ይታመናሉ። 6 በኀይልህ ተራራዎችን አጽንተሃል፤ ብርታትንም ታጥቀሃል። 7 ከባሕሩ መናወጥ የተነሣ የሚያስገመግመውን የማዕበል ድምፅ ጸጥ ታደርጋለህ፤ የሕዝቦችንም ሁከት ዝም ታሰኛለህ። 8 ስላደረግሃቸው ተአምራት ዓለም በሙሉ በፍርሃት ይዋጣል፤ በአንተ ድንቅ ሥራ ምክንያት ከምድር ዳርቻ እስከ ምድር ዳርቻ የእልልታ ድምፅ ይሰማል። 9 ዝናብን በማዝነብ ምድርን ትጐበኛለህ፤ ፍሬያማ በማድረግ ታበለጽጋታለህ፤ ምንጮችህን በውሃ ትሞላለህ፤ ለምድርም ሰብልን ትሰጣለህ። ይህንንም የምታደርገው እንዲህ ነው፤ 10 ለታረሱ ማሳዎች በቂ ዝናብ ትሰጣለህ፤ ወጣ ገባውን ታስተካክላለህ፤ ዐፈሩንም በካፊያ ታለሰልሳለህ፤ ቡቃያዎችም በቅለው እንዲያድጉ ታደርጋለህ። 11 በአንተ ቸርነት የሚገኘው መከር እንዴት ብዙ ነው! አንተ በምትገኝበት ቦታ ሁሉ ብዙ ሰብል አለ። 12 የግጦሽ ስፍራዎች በመንጋ የተሞሉ ይሆናሉ፤ ተራራዎችም ደስታን እንደ ልብስ ይለብሳሉ። 13 መስኮች የብዙ በጎች መሰማሪያ ይሆናሉ፤ ሸለቆዎች በሰብል ይሸፈናሉ፤ ሁሉም ደስ ብሎአቸው፥ በእልልታ ይዘምራሉ። |