Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


መዝሙር 64 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የመማጠኛ ጸሎት

1 አምላክ ሆይ! በችግሬ ምክንያት ወደ አንተ ስጸልይ ስማ፤ ከጠላት ማስፈራራትም ጠብቀኝ።

2 ከክፉዎች ምሥጢራዊ ሤራና ከክፉ አድራጊዎች ዕቅድ ጠብቀኝ።

3 እነርሱ ምላሳቸውን እንደ ሰይፍ ይስላሉ፤ እጅግ የከፋ ቃላትን እንደ ፍላጻ አነጣጥረው ይወረውራሉ።

4 እነርሱም ያለ ፍርሀት ንጹሑን ሰው ሸምቀው ይነድፉታል።

5 ክፉ ሤራ ለማቀነባበር እርስ በርሳቸው ይመካከራሉ፤ ወጥመዳቸውንም የት እንደሚዘረጉ ያቅዳሉ፤ ይህን ሁሉ ሲያደርጉ “ማንም ሊያየን አይችልም” ይላሉ።

6 እነርሱ ክፉ ዕቅድ ዐቀዱ፤ “በሐሳባቸውም የተቀናጀ ወንጀል እንሠራለን” ይላሉ፤ ይህም የሰው ልብና የሰው አእምሮ በተንኰል የተሞላ መሆኑን ያሳያል።

7 እግዚአብሔር ግን ፍላጻዎችን ወደ እነርሱ ይወረውራል፤ እነርሱም በድንገት ይቈስላሉ።

8 እግዚአብሔር ንግግራቸው በራሳቸው ላይ ተመልሶ እንዲወድቁ ያደርጋቸዋል። የሚያዩአቸው ሁሉ በፍርሃት ከእነርሱ ይሸሻሉ።

9 ሰዎች ሁሉ ይፈራሉ፤ ስለ እግዚአብሔር ሥራ ይናገራሉ፤ ስላደረገውም ነገር ያሰላስላሉ።

10 ጻድቃን በእግዚአብሔር ደስ ይበላቸው እርሱንም ከለላ ያድርጉ፤ ልባቸውም ቅን የሆነ ሁሉ ያመስግኑት።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos