መዝሙር 61 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየመማጠኛ ጸሎት 1 አምላክ ሆይ! ጩኸቴን አድምጥ፤ ጸሎቴንም ስማ። 2 ተስፋ ቈርጬ ሳለ ከሩቅ አገር ወደ አንተ እጮኻለሁ፤ ከእኔ በላይ ወደ አለው ከፍተኛ አምባ ምራኝ። 3 አንተ ጠባቂዬና ከጠላቶቼ የምከለልብህ ብርቱ መጠጊያዬ ነህ። 4 በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በቤትህ እንድኖርና በጥበቃህ ሥር መጠለያ እንዳገኝ ፍቀድልኝ። 5 አምላክ ሆይ! ስእለቴን ሰማህ፤ አንተን ለሚፈሩ ሰዎች ያዘጋጀኸውን በረከት ለእኔም ሰጠኸኝ። 6 በንጉሡ ዕድሜ ላይ ብዙ ዓመቶች ጨምርለት፤ ለብዙ ዘመንም እንዲኖር አድርገው! 7 አምላክ ሆይ! በፊትህ ለዘለዓለም እንዲነግሥ አድርገው፤ በዘለዓለማዊው ፍቅርህና በታማኝነትህ ጠብቀው። 8 ለአንተ የተሳልኩትን በየቀኑ በማቅረብ ዘወትር የምስጋና መዝሙር እዘምርልሃለሁ። |