መዝሙር 6 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 እግዚአብሔር ሆይ! በቊጣህ አትገሥጸኝ፤ በመዓትህም አትቅጣኝ። 2 እግዚአብሔር ሆይ! ደካማ ስለ ሆንኩ ምሕረት አድርግልኝ፤ ጌታ ሆይ! ደካማ ሰውነቴ እየተሠቃየ ስለ ሆነ፥ እባክህ ፈውሰኝ። 3 እግዚአብሔር ሆይ! ሰውነቴ በሙሉ እጅግ ታውኮአል፤ ታዲያ፥ እኔን ከመርዳት የምትዘገየው እስከ መቼ ነው? 4 እግዚአብሔር ሆይ! ተመልሰህ ታደገኝ፤ የዘለዓለም ፍቅርህን በማሳየት አድነኝ። 5 ከሞቱት መካከል አንድም የሚያስታውስህ የለም። በመቃብርስ ሆኖ የሚያመሰግንህ ማነው? 6 ከሐዘኔ ብዛት የተነሣ ደክሜአለሁ፤ ከለቅሶዬ ብዛት የተነሣ በየሌሊቱ አልጋዬ በእንባ ይረጥባል፤ ትራሴም ይርሳል። 7 ከጠላቶቼ ተቃውሞ የተነሣ በጣም በማልቀሴ ዐይኖቼ ፈዘዋል፤ ማየትም ተስኖኛል። 8 እግዚአብሔር የለቅሶዬን ጩኸት ሰምቶአል፤ ስለዚህ እናንተ ክፉ አድራጊዎች ከእኔ ወዲያ ራቁ! 9 እግዚአብሔር ልመናዬን ያዳምጣል፤ እግዚአብሔር ለጸሎቴ መልስ ይሰጣል። 10 ጠላቶቼ ሁሉ ያፍራሉ፤ በድንገትም ተዋርደው ወደ ኋላቸው ይሸሻሉ። |