መዝሙር 54 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምእነሆ፥ ዳዊት በእኛ ዘንድ ተሸሽጓል ብለው በነገሩት ጊዜ የዳዊት መዝሙር ከጠላት እጅ ለመዳን የቀረበ ጸሎት 1 አምላክ ሆይ! በስምህ አድነኝ፤ በኀይልህም ፍረድልኝ። 2 አምላክ ሆይ! ጸሎቴን ስማ! ቃሌንም አድምጥ። 3 ሞገደኞች አደጋ ሊጥሉብኝ ተነሡ፤ ጨካኞች ሊገድሉኝ ይፈልጋሉ፤ ስለ እግዚአብሔርም አያስቡም። 4 ነገር ግን አምላክ ረዳቴ ነው፤ ጌታም የሕይወቴ ደጋፊ ነው። 5 ተንኰላቸውን በሚያስጨንቁኝ ጠላቶቼ ላይ መልስባቸው፤ እነርሱን በማጥፋት ታማኝነትህን አሳይ። 6 መሥዋዕትህን በፍላጎቴ አቀርብልሃለሁ፤ እግዚአብሔር ሆይ፥ ተገቢ ስለ ሆነ ለስምህ ምስጋና አቀርባለሁ 7 ከችግሬ ሁሉ አድነኸኛል፤ የጠላቶቼንም ውድቀት አየሁ። |