መዝሙር 53 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየሰዎች ክፋት 1 ሞኞች በልባቸው “እግዚአብሔር የለም” ይላሉ፤ እንደነዚህ ያሉት ሰዎች የተበላሹ ናቸው፤ አጸያፊ ድርጊቶችንም ይፈጽማሉ፤ ከእነርሱ መካከል መልካም ነገርን የሚያደርግ አንድም የለም። 2 አስተዋዮችና እግዚአብሔርን የሚፈልጉ ሰዎች እንዳሉ ያይ ዘንድ እግዚአብሔር ከሰማይ ወደ ሰው ልጆች ተመለከተ። 3 ነገር ግን ሁሉም ባዝነዋል፤ ሁሉም በአንድነት ተበላሽተዋል፤ ከእነርሱ አንድ እንኳ መልካም ነገርን የሚያደርግ የለም። 4 እግዚአብሔር “ክፉ አድራጊዎች ከቶ አያስተውሉምን? ሰዎች እንጀራን እንደሚበሉ ክፉ አድራጊዎች ሕዝቤን ይበዘብዛሉ፤ እነርሱም ወደ እኔ ወደ እግዚአብሔር አይጸልዩም።” ይላል። 5 እግዚአብሔር የሕዝቡን ጠላቶች ስለ ሰባበራቸው ከምንጊዜውም ይልቅ በፍርሃት ተጨነቁ፤ እግዚአብሔርም ስለ ጠላቸው ፈጽሞ ያፍራሉ። 6 ምነው መዳን ለእስራኤል ከጽዮን በመጣ! እግዚአብሔር የሕዝቡን ምርኮ በሚመልስበት ጊዜ፥ የያዕቆብ ልጆች ደስ ይላቸዋል፤ የእስራኤል ሕዝብ ሐሴት ያደርጋሉ። |