መዝሙር 44 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየመማጠኛ ጸሎት 1 አምላክ ሆይ! በጥንት ዘመን ያደረግኸውን ሁሉ በጆሮአችን ሰማን፤ የቀድሞ አባቶቻችንም በዘመናቸው ስላደረግሃቸው ድንቅ ነገሮች ሁሉ ነግረውናል። 2 በቀድሞ ዘመን እጆችህ ያደረጉትን ድርጊት ሁሉ አባቶቻችን ነግረውናል፤ ይኸውም፥ እነርሱን ለመትከል ሕዝቦችን አባረሃል፤ እነርሱን ለማደላደል ነዋሪዎቹን አጥፍተሃል። 3 እነርሱ ምድርን የወረሱት በሰይፋቸው አይደለም፤ ድል አድርገው የወሰዱትም በራሳቸው ኀይል አይደለም፤ ይህን ሁሉ ያደረጉት አንተ ስለ ወደድካቸውና ከእነርሱም ጋር በመሆን በኀይልህና በብርታትህ ስለ ረዳሃቸው ነው። 4 አንተ ንጉሤና አምላኬ ነህ፤ የያዕቆብ ዘር ለሆነው ሕዝብህ፥ ድልን የምታጐናጽፍ አንተ ነህ። 5 በአንተ ርዳታ ጠላቶቻችንን ድል እንነሣለን፤ በስምህም ተቃዋሚዎቻችንን እንረግጣለን። 6 በቀስቴ አልተማመንም፤ ሰይፌም አያድነኝም። 7 ከጠላቶቻችን የምታድነን አንተ ነህ፤ የሚጠሉንንም የምታሳፍርልን አንተ ነህ። 8 አምላክ ሆይ! ዘወትር በአንተ እንመካለን፤ ስምህንም ለዘለዓለም እናመሰግናለን። 9 አሁን ግን ጣልከን፤ አዋረድከንም፤ ከሚዘምተው ሠራዊታችን ጋር አብረህ መውጣትን ትተሃል። 10 ከጠላቶቻችን ፊት እንድንሸሽ አደረግኸን፤ ጠላቶቻችንም ያለንን ሀብት ሁሉ ዘረፉን። 11 እንደሚታረዱ በጎች አደረግኸን፤ በአሕዛብ ምድር በተንከን። 12 ሕዝብህን በአነስተኛ ዋጋ ሸጥከው፤ እርሱንም በመሸጥ ምንም አላተረፍክም። 13 በጐረቤቶቻችን የምንነቀፍ አደረግኸን፤ በዙሪያችን ላሉትም መዘባበቻና መሳለቂያ አደረግኸን። 14 በሕዝቦች መካከል መተረቻ አደረግኸን፤ እነርሱም ራሳቸውን ይነቀንቁብናል። 15 ውርደቴ ዘወትር በፊቴ ነው፤ ፊቴንም ኀፍረት ሸፍኖታል። 16 እንዲህም የሆንኩት ጠላቶቼ በሚበቀሉኝ ጊዜ ሌሎች ሰዎች ሲያፌዙብኝና ሲሳለቁብኝ በመስማቴ ነው። 17 ይህም ሁሉ የደረሰብን አንተን ሳንረሳና ቃል ኪዳንህንም ሳናፈርስ ነው። 18 ልባችን ለአንተ እምነተቢስ አልሆነም፤ እግራችንም ከአንተ መንገድ አልወጣም። 19 ነገር ግን አራዊት በሚኖሩበት ስፍራ ሰብረኸናል። በድቅድቅ ጨለማም ሸፍነኸናል። 20 የአምላካችንን ስም ረስተን ቢሆን፥ ወደ ባዕዳን አማልክት እጆቻችንን ዘርግተን ቢሆን፥ 21 አንተ የተሰወረውን ሐሳባችንን ስለምታውቅ በደላችንን ገልጠህ ባየህብን ነበር። 22 ነገር ግን ስለ አንተ በየቀኑ እንገደላለን፤ እንደሚታረዱ በጎችም ተቈጥረናል። 23 ጌታ ሆይ! ንቃ! ስለምንስ ታንቀላፋለህ? ተነሥ! ለዘለዓለም አትተወን! 24 መጨቈናችንንና ችግራችንን ቸል በማለት ስለምን ከእኛ ትሰወራለህ? 25 መሬት እስክንነካ ድረስ አጐንብሰናል፤ በምድር ላይም ተዘርረናል። 26 ተነሥ እኛን ለመርዳት ና! ስለ ዘለዓለማዊው ፍቅርህም ተቤዠን! |