መዝሙር 4 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምእግዚአብሔርን በመታመን የሚቀርብ ጸሎት 1 አንተ የእውነት አምላክ ነህ፤ እባክህን ለጸሎቴ መልስ ስጠኝ! እኔ በጣም በጭንቀት ላይ ነበርኩ አንተ ግን ነጻ አወጣኸኝ፤ አሁንም ራራልኝና ጸሎቴን ስማ። 2 እናንተ ሰዎች፥ እስከ መቼ ክብሬን ታዋርዳላችሁ? እስከ መቼስ ከንቱ ነገርን ትወዳላችሁ? እስከ መቼስ ሐሰትን ትፈልጋላችሁ? 3 እግዚአብሔር ታማኞች የሆኑ ሰዎችን ለራሱ እንደ መረጠ ዕወቁ፤ ስለዚህ ወደ እርሱ በምጸልይበት ጊዜ ይሰማኛል። 4 ምንም ያኽል ብትበሳጩ ኃጢአት አትሥሩ፤ በምትተኙበት ስፍራ በጸጥታ ልባችሁን መርምሩ። 5 ለእግዚአብሔር ትክክለኛውን መሥዋዕት አቅርቡ፤ እምነታችሁንም በእርሱ ላይ አድርጉ። 6 “መልካሙን ነገር ማን ያሳየናል?” የሚሉ ብዙዎች ናቸው፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ሆይ! የፊትህ ብርሃን በእኛ ላይ ይብራ! 7 ሌሎች ከእህልና ከወይን ከሚያገኙት ደስታ ይልቅ አንተ በልቤ ያኖርከው ደስታ ይበልጣል። 8 እግዚአብሔር ሆይ! በሰላም እንድኖር የምታደርገኝ አንተ ብቻ ስለ ሆንክ እኔ በምተኛበት ጊዜ፥ በሰላም አንቀላፋለሁ። |