መዝሙር 3 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየስደት ጊዜ ጸሎት 1 እግዚአብሔር ሆይ! ጠላቶቼ እንዴት ብዙዎች ናቸው! ብዙዎችም በጠላትነት በእኔ ላይ ተነሥተዋል፤ 2 ብዙ ሰዎች “እግዚአብሔር አያድነውም” እያሉ ስለ እኔ ይናገራሉ። 3 እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ግን ጋሻዬ ነህ፤ ድልን በማጐናጸፍ ክብርን የምትሰጠኝ አንተ ነህ። 4 ድምፄን ከፍ አድርጌ ወደ እግዚአብሔር እጮኻለሁ፤ እርሱም በተቀደሰ ተራራው ላይ ሆኖ ይሰማኛል። 5 እኔ ተኛሁ፥ አንቀላፋሁም፤ እግዚአብሔር ሌሊቱን ሙሉ ስለ ጠበቀኝ ከእንቅልፌ ተነሣሁ። 6 በዙሪያዬ የከበቡኝን በብዙ ሺህ የሚቈጠሩትን ጠላቶቼን አልፈራቸውም። 7 ጌታ ሆይ! ተነሥ! አምላኬ ሆይ! መጥተህ አድነኝ! የጠላቶቼን መንጋጋ ስበር፤ ጥርሶቻቸውንም አድቅቅ። 8 ማዳን የእግዚአብሔር ነው፤ እግዚአብሔር ሆይ፥ በረከትህ በሕዝብህ ላይ ይሁን። |