መዝሙር 20 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምድል ለማግኘት የቀረበ ጸሎት 1 በችግር ቀን እግዚአብሔር ጸሎትህን ይስማ! የያዕቆብ አምላክም ስም ይጠብቅህ! 2 ከመቅደሱ ርዳታውን ይላክልህ፤ ከጽዮን ተራራም ይደግፍህ። 3 መባህን ሁሉ ይቀበልልህ፤ በመሥዋዕትህም ደስ ይበለው። 4 የልብህን ምኞት ይስጥህ፤ ሐሳብህን ሁሉ ይፈጽምልህ፤ 5 ድል በማድረግህ እልል እንላለን፤ በአምላካችንም ስም ዓርማችንን ከፍ እናደርጋለን፤ እግዚአብሔር ልመናህን ሁሉ ይፈጽምልህ። 6 እግዚአብሔር ቀብቶ ያነገሠውን እንደሚረዳ አሁን ዐውቃለሁ፤ በቀኝ እጁ ታላቅ ድልን በማቀዳጀት ከተቀደሰው ቦታ ከሰማይ ለጸሎቱ መልስ ይሰጠዋል። 7 አንዳንዶች በጦር ሠረገሎቻቸው፥ ሌሎችም በፈረሶቻቸው ይመካሉ፤ እኛ ግን በአምላካችን በእግዚአብሔር ኀይል እንታመናለን። 8 እነርሱ ተሰናክለው ይወድቃሉ፤ እኛ ግን እንነሣለን፤ ጸንተንም እንቆማለን። 9 አምላክ ሆይ! ንጉሡን ከጠላቶቹ እጅ አድነው፤ እኛም በምንጠራህ ጊዜ ስማን። |