መዝሙር 17 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 እግዚአብሔር ሆይ! ትክክለኛ ፍርድ ለማግኘት የማቀርብልህን ጸሎት ስማ፤ ጩኸቴንም አድምጥ፤ በሽንገላ ሳይሆን በእውነት የማቀርበውን ጸሎት ስማ። 2 ዐይኖችህ እውነትን ማየት ስለሚችሉ አንተ ብቻ ልትፈርድልኝ ትችላለህ። 3 ልቤን ብትመረምር፥ በሌሊት ብትጐበኘኝ፥ ብትፈትነኝም፥ ከእኔ ክፋትን አታገኝም፤ አንደበቴም አይስትም። 4 የሰዎችን ሥራ በሚመለከት፥ አንተ በተናገርከው ቃል መሠረት፥ እኔ ከዐመፀኞች አካሄድ ራሴን ጠብቄአለሁ። 5 ዘወትር በመንገድህ ተራመድኩ፤ ከመንገድህም ወጥቼ አልባዘንኩም። 6 አምላክ ሆይ! ልመናዬን ስለምትሰማ፥ ወደ አንተ እጸልያለሁ፤ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፤ ቃሌንም ስማ። 7 የአንተን ከለላ ለሚፈልጉ፥ በቀኝ እጅህ የምታድናቸው አምላክ ሆይ! ዘለዓለማዊ ፍቅርህን በአስደናቂ ሁኔታ ግለጥ። 8 የዐይን ብሌን በጥንቃቄ የሚጠበቀውን ያኽል ጠብቀኝ፤ በጥበቃህ ውስጥ ሰውረኝ። 9 ከበባ አድርገው ከሚያጠፉኝ ጨካኝ ጠላቶቼ ጠብቀኝ። 10 እነርሱ ለርኅራኄ ልባቸውን ዘግተዋል፤ አፋቸውም ትዕቢትን ይናገራል። 11 ጠላቶቼ አስጨነቁኝ፤ ከበባም አደረጉብኝ፤ ወደ መሬት ሊጥሉኝም ዐይናቸውን ጣሉብኝ። 12 እነርሱ እንደ ተራቡ አንበሶች ወይም እንደ ሸመቁ ደቦል አንበሶች ናቸው። 13 እግዚአብሔር ሆይ! ተነሥና ጣላቸው፤ በሰይፍህም ሕይወቴን ከክፉዎች አድን። 14 እግዚአብሔር ሆይ! የሕይወታቸው ድርሻ የዚህ ዓለም ነገር ብቻ ከሆነ ሰዎች በእጅህ አድነኝ፤ ለምትወዳቸው ምግብን ስጣቸው፤ ልጆቻቸው ብዙ ይኑራቸው፤ የልጅ ልጆቻቸውም የተትረፈረፈ ምግብ እንዲኖራቸው አድርግ። 15 እኔ በጽድቅ ፊትህን አያለሁ፤ በምነቃበት ጊዜም የአንተን አምሳያ በማየቴ እደሰታለሁ። |