መዝሙር 16 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየእግዚአብሔርን አለኝታ ለማግኘት የቀረበ ጸሎት 1 አምላክ ሆይ! የምታመነው በአንተ ስለ ሆነ ጠብቀኝ፤ 2 እግዚአብሔርን “አንተ ጌታዬ ነህ፤ ያለኝ መልካም ነገር ሁሉ ያንተ ስጦታ ነው” አልኩት። 3 በምድር ላይ የሚኖሩ ቅዱሳን የተከበሩ ናቸው፤ በእነርሱም እደሰታለሁ። 4 ሌሎች አማልክትን የሚያመልኩ ብዙ ሐዘን ይደርስባቸዋል፤ እኔ እንደነዚህ ላሉት አማልክት የደም መሥዋዕትን አላቀርብም፤ እነርሱንም አላመልክም። 5 እግዚአብሔር ሆይ! ዕድል ፈንታዬና ጽዋዬ አንተ ነህ፤ ድርሻዬንም አስተማማኝ ታደርገዋለህ። 6 ለእኔ የተለኩልኝ የድንበር መስመሮች ያረፉት በሚያስደስቱ ቦታዎች ላይ ነው፤ በእርግጥ እኔ የሚያስደስት ርስት አለኝ። 7 የሚመክረኝን እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤ በሌሊት እንኳ ሕሊናዬ ያስተምረኛል። 8 ዘወትር እግዚአብሔርን አስቀድማለሁ፤ እርሱም በቀኜ ስለ ሆነ አልታወከም። 9 ስለዚህ ልቤ ተደስቶ ይፈነጥዛል፤ ሰውነቴም ያለ ስጋት ያርፋል። 10 ነፍሴን በሲኦል አትተዋትም፤ ታማኝህንም መበስበስ እንዲደርስበት አታደርግም። 11 የሕይወትን መንገድ ታሳየኛለህ፤ በአንተ ፊት ሙሉ ደስታ፥ በቀኝህም የዘለዓለም እርካታ ይገኛል። |