መዝሙር 140 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየእግዚአብሔርን ጠባቂነት ለማግኘት የቀረበ ጸሎት 1 እግዚአብሔር ሆይ! ከክፉ ሰዎች አድነኝ፤ ከዐመፀኞች እጅም ጠብቀኝ። 2 የእነርሱ ልብ ክፉ ዕቅዶችን ያቅዳል፤ ዘወትርም ጥልን ያነሣሣሉ። 3 ምላሳቸው እንደ መርዛም እባብ ተናዳፊ ነው፤ ቃላቸውም እንደ እፉኝት መርዝ ነው። 4 እግዚአብሔር ሆይ! ከክፉዎች ኀይል ጠብቀኝ፤ እኔን ለመጣል ከሚያቅዱ ከዐመፀኞች ሰዎች ጠብቀኝ። 5 ትምክሕተኞች ወጥመድ ዘረጉብኝ፥ እንደ መረብ የተጠላለፈ ገመድም ዘረጉብኝ። እኔንም ለመያዝ በመንገዴ ላይ ወጥመድ አጠመዱ። 6 እግዚአብሔርን “አንተ አምላኬ ነህ” እለዋለሁ፤ እግዚአብሔር ሆይ! ምሕረትህን ለማግኘት ስጸልይ ስማኝ! 7 ኀያሉ አዳኜ ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ! በጦርነት ቀን ራሴን እንደ ጋሻ ሸፍንልኝ። 8 ለክፉዎች የሚፈልጉትን ነገር አትስጣቸው፤ ዕቅዳቸው እንዲሰምር አታድርግ። 9 የከበቡኝ ጠላቶቼ በእኔ ላይ ያቀዱትን ሤራ በእነርሱ ላይ እንዲፈጸም አድርግ። 10 የእሳት ፍም በላያቸው ይውደቅ፤ ወደ ጒድጓድም ይጣሉ፤ ከዚያም ከቶ አይውጡ። 11 ሌሎችን በሐሰት የሚከስሱ በምድር ላይ ጸንተው አይኑሩ፤ ክፉ ነገር በጨካኞች ሰዎች ላይ ይድረስ፤ ይደምስሳቸውም። 12 እግዚአብሔር ሆይ! ለድኾች እንደምትፈርድ፥ ለተጨቈኑትም መብታቸውን እንደምታስከብር ዐውቃለሁ። 13 ደጋግ ሰዎች በእውነት ያመሰግኑሃል፤ በፊትህም ጸንተው ይኖራሉ። |