መዝሙር 14 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየሰዎች ክፋት 1 ሞኞች በልባቸው፦ “እግዚአብሔር የለም” ይላሉ፤ እንደነዚህ ያሉት የተበላሹ ናቸው፤ አጸያፊ ድርጊቶችንም ይፈጽማሉ፤ ከእነርሱ መካከል መልካም ነገርን የሚያደርግ አንድም የለም። 2 አስተዋዮችና አምላክን የሚፈልጉ ሰዎች እንዳሉ ያይ ዘንድ፥ እግዚአብሔር ከሰማይ ወደታች ወደ ሰው ልጆች ተመለከተ። 3 ነገር ግን ሁሉም ባዝነዋል፤ ሁሉም በአንድነት ተበላሽተዋል፤ ከእነርሱ አንድ እንኳ መልካም ነገርን የሚያደርግ የለም። 4 “እግዚአብሔር ክፉ አድራጊዎች ከቶ አያስተውሉምን? ሰዎች እንጀራን እንደሚበሉ ክፉ አድራጊዎች ሕዝቤን ይበዘብዛሉ፤ እነርሱም ወደ እኔ ወደ እግዚአብሔር አይጸልዩም።” ይላል። 5 እግዚአብሔር የሚገኘው ከጻድቃን ጋር ስለ ሆነ እነርሱ በፍርሃት ይሸበራሉ። 6 እናንተ የድኾችን ዕቅድ ብታሰናክሉም እንኳ እግዚአብሔር ለእነርሱ መጠጊያቸው ይሆናል። 7 ምነው መዳን ለእስራኤል ከጽዮን በመጣ! እግዚአብሔር የሕዝቡን ምርኮ በሚመልስበት ጊዜ፤ የያዕቆብ ልጆች ይደሰታሉ፤ የእስራኤል ሕዝብ ሐሴት ያደርጋሉ። |