Biblia Todo Logo
La Biblia Online

- Anuncios -


መዝሙር 139 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የእግዚአብሔር ፍጹም እውነትና እንክብካቤ

1 እግዚአብሔር ሆይ! መርምረህ ዐውቀኸኛል።

2 አንተ ስቀመጥም ሆነ ስነሣ ታውቃለህ፤ ሐሳቤን ሁሉ ከሩቅ ሆነህ ታስተውላለህ።

3 የምጓዝበትንና የማርፍበትን ቦታ ታስተውላለህ፤ ተግባሬን ሁሉ ታውቃለህ።

4 እግዚአብሔር ሆይ! ገና ከመናገሬ በፊት ምን ለማለት እንደማስብ ታውቃለህ።

5 በዙሪያዬ ሁሉ ትገኛለህ፤ በኀይልህም ትጠብቀኛለህ።

6 የአንተ ዕውቀት እጅግ ጥልቅ ነው፤ እኔ ላስተውለው ከምችለው በላይ ነው።

7 ከአንተ ለማምለጥ ወዴት መሄድ እችላለሁ? ከፊትህስ ርቄ ወዴት እሸሻለሁ?

8 ወደ ሰማይ ብወጣ እዚያ ትገኛለህ፤ ወደ ሙታን ዓለም ብወርድ በዚያም አንተ አለህ።

9 ከፀሐይ መውጫ ባሻገር በርሬ ብሄድ፥ ወይም በፀሐይ መግቢያ በኩል ርቄ ብኖር፥

10 እዚያ ተገኝተህ በእጅህ ትመራኛለህ፤ በቀኝ እጅህም ትደግፈኛለህ።

11 ጨለማን “ሰውረኝ” ወይም ብርሃንን “ወደ ሌሊት ተለወጥልኝ” ብል

12 ጨለማ እንኳ በአንተ ዘንድ አይጨልምም፤ ሌሊቱም የቀን ያኽል ያበራል፤ ስለዚህ በአንተ ዘንድ ጨለማና ብርሃን ልዩነት የላቸውም።

13 ሁለንተናዬን የፈጠርክ አንተ ነህ፤ በእናቴ ማሕፀን አገጣጥመህ የሠራኸኝ አንተ ነህ።

14 በሚያስፈራና በሚያስገርም ሁኔታ ስለ ተፈጠርኩ አመሰግንሃለሁ፤ ሥራዎችህ ሁሉ አስደናቂዎች መሆናቸውን ጠንቅቄም ዐውቃለሁ።

15 በድብቁ ቦታ በተሠራሁ ጊዜና በጥልቁ መሬት ውስጥ በአንድነት በተገጣጠምኩ ጊዜ ሰውነቴ ለአንተ ድብቅ አልነበረም።

16 ከመወለዴ በፊት አየኸኝ፤ ለእኔ የተወሰኑልኝ ቀኖቼ ገና ከመጀመራቸው በፊት በመዝገብህ ሰፍረዋል።

17 አምላክ ሆይ! ሐሳብህ እጅግ የከበረና የሰፋ ስለ ሆነ እኔ ልረዳው አልችልም።

18 ሐሳብህ ቢቈጠር ከባሕር አሸዋ የበዛ ነው፤ ቈጥሬ ልጨርስ ብፈልግ ዘለዓለማዊ መሆን ይኖርብኛል።

19 አምላክ ሆይ! ምነው ክፉዎችን ባጠፋህ! ምነው የደም ሰዎችንም ከእኔ ባራቅህ!

20 እነርሱ በአንተ ላይ ክፉ ነገር ይናገራሉ፤ በጠላትነትም ስምህን በክፉ ያነሣሉ።

21 እግዚአብሔር ሆይ! የሚጠሉህን እጅግ እጠላቸዋለሁ! በአንተ ላይ የሚያምፁትንም እጅግ እጸየፋቸዋለሁ!

22 በብርቱ እጠላቸዋለሁ፤ እንደ ጠላቶቼም እቈጥራቸዋለሁ።

23 አምላክ ሆይ! መርምረኝ፤ ልቡናዬንም ዕወቅ፤ ፈትነኝ፤ ሐሳቤንም ዕወቅ።

24 በእኔ ውስጥ በደል እንዳለ ተመልከት፤ በዘለዓለማዊውም መንገድ ምራኝ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos