መዝሙር 135 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየምስጋና መዝሙር 1 እግዚአብሔርን አመስግኑ! እናንተ የእግዚአብሔር አገልጋዮች፥ ስሙን አመስግኑ! 2 በአምላካችን መቅደስ፥ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ የምትቆሙ ሁሉ አመስግኑት! 3 ደግ ስለ ሆነ እግዚአብሔርን አመስግኑ! ቸር ስለ ሆነ ለስሙ ዘምሩ! 4 እግዚአብሔር ያዕቆብን ለራሱ፥ የእስራኤልንም ሕዝብ የግሉ አድርጎ መረጠ። 5 እግዚአብሔር ከአማልክት ሁሉ የሚበልጥ ታላቅ አምላክ መሆኑን ዐውቃለሁ። 6 በሰማይና በምድር፥ በጥልቅ ባሕሮችም የወደደውን ሁሉ ያደርጋል። 7 ዝናብ ያዘለ ደመናን ከምድር ዳርቻ ያመጣል፤ በዝናብ ጊዜ መብረቅ እንዲኖር ያደርጋል፤ ነፋስንም ከቦታው ያወጣዋል። 8 በግብጽ አገር የሰዎችንና የእንስሶችን የበኲር ልጆችን የገደለ እርሱ ነው። 9 በዚያ ንጉሡን ፈርዖንንና አገልጋዮቹን ሁሉ ለመቅጣት ተአምራትንና ድንቅ ነገሮችን አደረገ። 10 ብዙ የአሕዛብ መንግሥታትን ደመሰሰ፤ ኀያላን ነገሥታትንም ገደለ። 11 የአሞራውያንን ንጉሥ ሲሖንን፥ የባሳንንም ንጉሥ ዖግን፥ የከነዓንንም ነገሥታት ሁሉ ገደለ። 12 ምድራቸውንም ለሕዝቡ ለእስራኤል ርስት አድርጎ ሰጠ። 13 እግዚአብሔር ሆይ! ስምህ ዘወትር ሲታወጅ ይኖራል፤ ትውልድ ሁሉ ያስታውሱሃል። 14 እግዚአብሔር ለሕዝቡ ይፈርዳል፤ ለአገልጋዮቹም ይራራል። 15 የአሕዛብ አማልክት ከብርና ከወርቅ በሰው እጅ የተሠሩ ጣዖቶች ናቸው። 16 አፍ አላቸው፤ አይናገሩም፤ ዐይን አላቸው፤ አያዩም። 17 ጆሮ አላቸው፤ አይሰሙም፤ በአፍንጫቸውም መተንፈስ አይችሉም። 18 የሠሩአቸውና የሚታመኑባቸው ሁሉ እንደነዚህ ጣዖቶች ናቸው። 19 የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! እግዚአብሔርን አመስግኑ! እናንተም የእግዚአብሔር ካህናት እግዚአብሔርን አመስግኑ! 20 እናንተ ሌዋውያን እግዚአብሔርን አመስግኑ! እግዚአብሔርን የምታከብሩ ሁሉ እግዚአብሔርን አመስግኑ! 21 እግዚአብሔርን በጽዮን አመስግኑት! በመኖሪያው በኢየሩሳሌም አመስግኑት! እግዚአብሔርን አመስግኑ! |